በላጩ ዚክር: ሱብሓነላህ፣ አልሐምዱሊላህ፣ ላ ኢላሀ ኢለላህ

በቀኑ በማንኛውም ጊዜ የሚባሉ፣ ታላቅ ምንዳ ያላቸው አጫጭር ዚክሮች።

1 አንድ ጊዜ

لَا إِلَهَ إِلَّا اللَّهُ

ትርጉም እና ምንጭ

ጃቢር ረዲየሏሁ ዐንሁ እንዲህ ማለቱ ተላልፏል፡ "የአሏህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ፡ "በላጩ ዚክር 'ላ ኢላሃ ኢለሏህ' ማለት ሲሆን በላጩ ዱዓእ ደግሞ 'አልሐምዱሊላህ' ማለት ነው።'"

ቲርሚዚ፣ ነሳኢ በኩብራ ውስጥ፣ ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል። ደረጃ: ሐሰን ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና በላጩ ዚክር "ላ ኢላሃ ኢለሏህ" - ትርጉሙም፡ ከአሏህ በቀር በእውነት አምልኮ የሚገባው የለም - መሆኑን፤ ከዱዓእ በላጩ ደግሞ "አልሐምዱሊላህ" - ትርጉሙም፡ ፀጋንም የሚውለው ለተሟላ ውብ መገለጫም የተገባው እርሱ አላህ ብቻ መሆኑን ማመን - እንደሆነ ተናገሩ።

ጥቅሞች

  • አሏህን በተውሒድ ቃል ማስታወስና በምስጋና ቃል መማፀን ማብዛት መበረታታቱን እንረዳለን።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

2 አንድ ጊዜ

سُبْحَانَ اللَّهِ، وَالْحَمْدُ لِلَّهِ، وَلَا إِلَهَ إِلَّا اللَّهُ، وَاللَّهُ أَكْبَرُ

ትርጉም እና ምንጭ

ከሰሙረህ ቢን ጁንዱብ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል: "አላህ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ንግግሮች አራት ናቸው። 'ሱብሓነላህ' (አላህ ሆይ! ጥራት ተገባህ) 'አልሐምዱ ሊላህ' (ምስጋና ለአላህ የተገባ ነው።) 'ላኢላሃ ኢለላህ' (ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም) 'አሏሁ አክበር' (አላህ ታላቅ ነው።) በማንኛቸውም ብትጀምር አይጎዳህም።"

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አላህ ዘንድ ተወዳጅ ንግግሮች አራት መሆናቸውን ተናገሩ:

"ሱብሓነላህ": ማለትም አላህን ከሁሉም ጉድለት ማጥራት ነው።

"አልሐምዱ ሊላህ": አላህን ከመውደድና ከማላቅ ጋር በምሉዕነት ባህሪ መግለፅ ነው።

"ላኢላሃ ኢለላህ": ማለትም ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም።

"አላሁ አክበር": ማለትም አላህ ከሁሉም ነገር የበለጠ ታላቅና ሀያል ነው።

ትሩፋቷንና ምንዳዋን ለማግኘት የቃላቱን ቅደም ተከተል መጠበቅ ግዴታ አይደለም።

ጥቅሞች

  • በማንኛውም ቃል መጀመር ምንም ችግር አለማሳደሩ ሸሪዓ ገር መሆኑን ያስረዳናል።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

3 አንድ ጊዜ

سُبْحَانَ اللَّهِ وَبِحَمْدِهِ، سُبْحَانَ اللَّهِ الْعَظِيمِ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሁረይራ -አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና- እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል: "ለምላስ ቀላል የሆኑ፣ ሚዛን ላይ የሚከብዱ፣ አርራህማን ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ሁለት ቃላቶች አሉ: ' 'ሱብሓነላሂ አልዐዚም ሱብሓነላሂ ወቢሐምዲሂ።'"

ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የሰው ልጅ ያለምንም መጨናነቅና በማንኛውም ሁኔታ ላይ ሆኖ ስለሚናገራቸው ሁለት ቃላቶች ነገሩን። እነሱም ምንዳቸው ሚዛን ላይ የገዘፈ፣ ጌታችን አር‐ራሕማንም የሚወዳቸው ናቸው።

"ሱብሓነላሂ አልዐዚም ሱብሐነላሂ ወቢሐምዲሂ" የሚሉት ናቸው። ደረጃቸው የላቀበትም ምክንያት የአላህን የልቅናና የምሉዕነት ባህሪያት የያዙ ፤ የላቀውንና የጠራውን አላህንም ከጉድለቶች ስለሚያጠሩ ነው።

ጥቅሞች

  • በላጩ ውዳሴ አላህን ማጥራትና ማወደስን የሰበሰበ ውዳሴ ነው።
  • አላህ በጥቂት ስራ ብዙ ምንዳ መመንዳቱ በባሮቹ ላይ ያለው እዝነት ሰፊ መሆኑን ይገልፅልናል።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

4 አንድ ጊዜ

سُبْحَانَ اللَّهِ، وَالْحَمْدُ لِلَّهِ، وَلَا إِلَهَ إِلَّا اللَّهُ، وَاللَّهُ أَكْبَرُ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሁረይራ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ ብሏል: "የአላህ መልዕክተኛ ሶለሏሁ ዓለይሂ ወስለም እንዲህ ብለዋል፡ ''ሱብሓነሏህ ወልሐምዱሊላህ ወላኢላሃ ኢለሏህ ወሏሁ አክበር' ማለቴ ፀሀይ የወጣችበት ክልል ሁሉ (ከሚሰጠኝ) የበለጠ ወደእኔ እጅግ ተወዳጅ ነው።'"

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በነዚህ ትላልቅ ቃላቶች አላህን ማወደስ ከዱንያና በውስጧ ካለው ሁሉ የተሻለ መሆኑን ተናገሩ። እነሱም:

"ሱብሓነሏህ" ይህም አላህን ከጉድለት ማጥራት ነው።

"አልሐምዱሊላህ" ይህም አላህን ከመውደድና ከማላቅ ጋር በምሉዕ ባህሪያቶቹ ማወደስ ነው።

"ላኢላሃ ኢለሏህ" ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም።

"አሏሁ አክበር" አላህ ከሁሉም ነገር የበለጠ ታላቅ ነው ማለት ነው።

ጥቅሞች

  • አላህን በማውሳት ላይ መነሳሳቱ። አላህን ማውሳት ፀሀይ የወጣችበት ክልል ሁሉ ከሚሰጠን የበለጠ ተወዳጅ ነውና።
  • ውዳሴ ማብዛት ደረጃና ምንዳ ስላለው በርሱ ላይ መነሳሳቱን እንረዳለን።
  • የዱንያ መጣቀሚያ ትንሽ ነው። ስሜትን የሚያስደስቱ ነገሮቿ ጠፊ ናቸው።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

5 100 ጊዜ

سُبْحَانَ اللَّهِ وَبِحَمْدِهِ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሁረይራ -አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦ "በቀን ውስጥ መቶ ጊዜ ሱብሓነላሂ ወቢሐምዲሂ "ጥራት ምስጋና ለአላህ ይገባው።" ያለ ሰው (የወንጀሉ ብዛት) የባህር ዓረፋ አምሳያ ቢሆን እንኳ ወንጀሉ ይታበስለታል።"

ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

በቀን ውስጥ መቶ ጊዜ "ሱብሓነሏሂ ወቢሐምዲሂ" (ጥራት ምስጋና ለአላህ ይገባው።) ያለ ሰው ባህር በሚናወጥ ወቅት ከላዩ እንደሚንጣለለው ነጭ አረፋ አምሳያ ወንጀሉ የበዛ ቢሆን እንኳ ወንጀሉ ይማራል ይታበሳል ብለው ነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ተናገሩ።

ጥቅሞች

  • ይህን ምንዳ የሚያገኘው በቀን ውስጥ አከታትሎም ይሁን በተለያየ ጊዜ እነዚህን ቃላት ያለ ሰው ነው።
  • ተስቢሕ ማለት: - አላህን ከጉድለት ማጥራት ሲሆን ፤ ሐምድ ማለት ደግሞ አላህን ከመውደድና ከማላቅ ጋር በምሉዕነት መግለፅ ነው።
  • በሐዲሡ ወንጀልን ማስማር ከሚለው የተፈለገበት ትናንሽ ወንጀሎችን ብቻ ነው። ትላልቅ ወንጀሎች ግን የግድ ተውበት ያስፈልጋቸዋል።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

6 አንድ ጊዜ

سُبْحَانَ اللَّهِ الْعَظِيمِ وَبِحَمْدِهِ

ትርጉም እና ምንጭ

ከጃቢር (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው: ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንዲህ ብለዋል: "ሱብሓነሏሂል ዐዚም ወቢሐምዲሂ ያለ ሰው ጀነት ውስጥ ለርሱ የተምር ዛፍ ይተከልለታል።"

ቲርሚዚ ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና (ሱብሓነሏሂ) አላህ ጥራት የተገባው ነው። (አልዐዚም) በዛቱ፣ በባህሪያቱና በድርጊቱ ታላቅ ነው። (ወቢሐምዲህ) የምሉዕነት መገለጫዎቹን ማስጠጋት አቆራኝቼ አጠራዋለሁ ያለ ሰው ይህቺን ውዳሴ ባለ ቁጥር በጀነት መሬት ላይ የተምር ዛፍ ይተከልለታል አሉ።

ጥቅሞች

  • አላህን ማውሳት በማብዛት ላይ መነሳሳቱን እንረዳለን። ከነዚህም ዚክሮች መካከል ከማመስገን ጋር ማጥራት አንዱ ነው።
  • ጀነት ሰፊ ናት። የጀነት ተክሎችም ተስቢሕ (ሱብሓነሏህ)ና ተሕሚድ (አልሐምዱሊላህ) ናቸው። ይህም በአላህ ፀጋና ችሮታ ነው።
  • ሐዲሡ ውስጥ ከሌሎች ዛፎች ተለይቶ የተምር ዛፍ የተጠቀሰው ጥቅሙ የበዛና ፍሬው ጣፋጭ ስለሆነ ነው። ስለዚህም አላህ ቁርአን ውስጥ አማኞች በእምነታቸው ላይ ያላቸውን ምሳሌ በተምር ዛፍ ነው የመሰለው።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

7 አንድ ጊዜ

لَا إِلَهَ إِلَّا اللهُ وَحْدَهُ لَا شَرِيكَ لَهُ، اللهُ أَكْبَرُ كَبِيرًا، وَالْحَمْدُ لِلَّهِ كَثِيرًا، سُبْحَانَ اللهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ، لَا حَوْلَ وَلَا قُوَّةَ إِلَّا بِاللهِ الْعَزِيزِ الْحَكِيمِ

ትርጉም እና ምንጭ

ከሰዕድ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: "አንድ የገጠር ሰው ወደ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና በመምጣት እንዲህ አለ: 'የምለውን ቃላት አስተምሩኝ?' እርሳቸውም 'ላኢላሃ ኢለሏህ ወሕደሁ ላሸሪከ ለህ፤ አሏሁ አክበር ከቢራ፣ ወልሐምዱሊላሂ ከሢራ፣ ወሱብሓነሏሂ ረቢል ዓለሚን፣ ላሐውለ ወላ ቁወተ ኢላ ቢላሂል ዐዚዚል ሐኪም በል።' አሉት። (ትርጉሙም: ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ የለም፤ ብቸኛና አጋር የሌለው ነው። አላህ እጅግ ታላቅ ነው፤ ለአላህ ብዙ ምስጋና የተገባው ነው፤ የዓለማቱ ጌታ አላህ ጥራት የተገባው ነው፤ አሸናፊና ጥበበኛ ከሆነው ከአላህ በቀር ሀይልም ብልሀትም የለም።) እርሱም 'እነዚህ ቃላት ጌታዬን (የማወድስበት) ናቸው። ለኔስ (የምለምንበት)?' አላቸው። እርሳቸውም 'አላሁመጝፊር ሊ ወርሐምኒ ወህዲኒ ወርዙቅኒ። በል!' አሉት።" (ትርጉሙም: አላህ ሆይ! ማረኝ፣ እዘንልኝ፣ ምራኝ፣ ሲሳይን ለግሰኝ።)

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

አንድ የገጠር ነዋሪ የሆነ ሰውዬ የአላህን መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) የሚናገረውን ውዳሴ እንዲያስተምሩት ጠየቃቸው። ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ለርሱ እንዲህ አሉት: "እንዲህ በል! "ላኢላሃ ኢለሏህ ወሕደሁ ላሸሪከ ለህ" በተውሒድ የምስክር ቃል ጀመሩ። (ትርጉሙም: ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ የለም፤ ብቸኛና አጋር የሌለው ነው።) "አሏሁ አክበር ከቢራ" ማለትም "አላህ ከሁሉም ነገር የበለጠ እጅግ ታላቅ ነው።" ማለት ነው። "ወልሐምዱ ሊላሂ ከሢራ" ማለትም "ለአላህ በባህሪዎቹ፣ በድርጊቶቹ፣ በማይቆጠሩ ፀጋዎቹ ብዙ ምስጋና የተገባው ነው።" ማለት ነው። "ሱብሐነሏሂ ረቢል ዓለሚን" ማለትም "አላህ ከጉድለት የጠራ የፀዳ ነው።" ማለት ነው። "ላሐውለ ወላ ቁወተ ኢላ ቢላሂል ዐዚዚል ሐኪም" ማለትም "በአላህ እገዛና መግጠም ካልሆነ በቀር ከአንድ ሁኔታ ወደ ሌላ ሁኔታ መለወጥ የለም።" ማለት ነው። ሰውዬውም "እነዚህ ቃላት ጌታዬን ለማውሳትና ለማላቅ ነው። ለነፍሴ የማደርገው ዱዐስ?" ብሎ ጠየቃቸው። ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ለርሱ "እንዲህ በል!" አሉት። "አልላሁመጝፊርሊ" (አላህ ሆይ! ማረኝ) ወንጀሎችን በመማርና በመሸሸግ "ወርሐምኒ" (እዘንልኝ) ሃይማኖታዊና ዱንያዊ ጥቅሞችን ለኔ በማድረስ እዘንልኝ። "ወህዲኒ" (ምራኝ!) ወደ ተሻለ ሁኔታና ቀጥተኛውን መንገድ ምራኝ። "ወርዙቅኒ" (ሲሳይን ለግሰኝ!) ሐላል ገንዘብን፣ ጤናን፣ ሁሉንም መልካምና ደህንነት ለግሰኝ።

ጥቅሞች

  • አላህን በ"ተህሊል"፣ በ"ተክቢር"፣ በ"ተሕሚድ"ና በ"ተስቢሕ" በማውሳት ላይ መነሳሳቱን እንረዳለን።
  • ከዱዓእ በፊት አላህን ማውሳትና ማወደስ እንደሚወደድ እንረዳለን።
  • የሰው ልጅ በምርጥ ዱዓ፣ በቁርአንና በሐዲሥ በመጡ ዱንያዊና አኺራዊ መልካም ነገሮችን የሰበሰቡ በሆኑ ዱዓዎች ማድረጉ እንደሚወደድ እንረዳለን። በፈለገው ዱዓ ማድረግም ይችላል።
  • አንድ ባሪያ ለዱንያውና አኺራው የሚጠቅመውን ነገር በመማር ላይ መጓጓት ይገባዋል።
  • ምህረትን፣ እዝነትንና ሲሳይን በመፈለግ ላይ መነሳሳቱን እንረዳለን። እነዚህ ጉዳዮችም የመልካም ነገሮች መሰብሰቢያ ናቸው።
  • ነቢዩ ( የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ለኡመታቸው የሚጠቅማቸውን ነገር በማስተማር ላይ መራራታቸውን እንረዳለን።
  • ከምህረት መለመን በኋላ እዝነትን መለመን የተወሳው ንፅህናው እንዲሟላ ነው። ምህረት ማለት ወንጀልህ መሸሸጉ፣ መታበሱና ከእሳት መዳን ሲሆን እዝነት ደግሞ መልካምን ማግኘትና ጀነት መግባት ነው። ትልቁ ስኬት ይህ ነው።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

8 አንድ ጊዜ

رَضِيتُ بِاللَّهِ رَبَّاً، وَبِالْإِسْلَامِ دِيناً، وَبِمُحَمَّدٍ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ نَبِيّاً

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሰዒድ አልኹድሪይ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው: የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንዲህ ብለዋል: "በአላህ ጌትነት፣ በእስልምና ሃይማኖትነት፣ በሙሐመድ መልክተኝነት ወድጃለሁ ያለ ሰው ጀነት ለርሱ ፀንታለታለች።"

አቡዳውድ ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) (ረዲቱ ቢላሂ ረብበን) በአላህ አምላክነት፣ ተንከባካቢነት፣ ንጉስነት፣ አለቃነት፣ አስተካካይነት ወድጃለሁ፤ (ወቢልኢስላሚ) በእስልምና በሁሉም ትእዛዛዊና ክልከላዊ ህግጋቶቹ (ዲነን) መንገድነት፣ ሃይማኖትነትና እምነትነት ወድጃለሁ፤ (ወቢሙሐመደን ረሱላ) በሙሐመድ ነቢይነት፣ እርሳቸው በተላኩበትና ወደኛ ባደረሱት ነገር ሁሉ ወድጃለሁ ያለ ሰው ጀነት ለርሱ እንደፀናችለት ተናገሩ።

ጥቅሞች

  • ይህን ዱዓ በማለት ላይ መነሳሳቱንና ይህንን ዱዓ ማለትን ተከትሎ የሚገኘው ምንዳ መገለፁን እንረዳለን።
  • በአላህ ጌትነት መውደድ ሲባል ሰውዬው ከአላህ ሱብሓነሁ ውጪ ያለን አለመገዛቱንም ያካትታል።
  • በሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ነቢይነትና መልክተኝነት መውደድም ነቢዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) መታዘዝና ለሱናቸው ተገዢ መሆንን ያካትታል።
  • በእስልምና ሃይማኖትነት መውደድ ሲባል አላህ ለባሮቹ የመረጠውን መውደድ ማለት ነው።
  • በሌላ ዘገባ እንደመጣው አዛን በሚባልበት ጊዜ ሁለቱን የምስክርነት ቃላት ካለ በኋላ ይህን ዱዓ ማለት ይወደዳል።
  • በሌላ ሐዲሥ እንደመጣው ደሞ ይህን ዱዓ ንጋትና ምሽት ላይ ማለትም ይወደዳል።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

9 አንድ ጊዜ

ትርጉም እና ምንጭ

አቢ ማሊክ አልአሽዐሪይ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንዲህ ብለዋል፦ የአላህ መልክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና እንዲህ አሉ: "ንፅህና የኢማን ግማሽ ነው 'አልሐምዱ ሊላህ' (ምስጋና ለአላህ የተገባ ነው) የሚለው ሚዛን ይሞላል፤ 'ሱብሐነላህ ወል'ሐምዱ ሊላህ' (አላህ ጥራት የተገባው ነው፤ ምስጋናም ሁሉ ለአላህ ነው) የሚለው በሰማያትና በምድር መካከል ያለውን ይሞላሉ ወይም ይሞላል ፤ ሰላት ብርሃን ነው፣ ምጽዋት ማስረጃ ነው፣ ትዕግስት ወገግታ (አንፀባራቂ ብርሃን) ነው፣ ቁርኣን ላንተ ወይም በአንተ ላይ ማስረጃ ነው። ሁሉም ሰው በማለዳ ወጥቶ ነፍሱን ይሸጣል። ወይ ከጥፋት ነፃ ያወጣታል ወይም ወደ ጥፋት ይጥላታል። "

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ውጫዊ ንፅህና በውዱ እና በገላ ትጥበት የሚተገበር እንደሆነና የሰላት ቅድመ መስፈርት እንደሆነም ይነግሩናል ። "አልሐምዱሊላህ ሚዛንን ትሞላለች " የሚለው ነቢያዊ ንግግር :- ጥራት ይገባውና አላህን ማወደስ እንዲሁም ምሉዕ በሆኑ ባህሪያቶች እሱን መግለፅ፥ የትንሳኤ ቀን ስትመዘን የስራዎችን ሚዛን ትሞላለች ማለት ነው። "ሱብሐነላህ ወልሐምዱሊላህ " የሚለውን መናገር አላህን ከሁሉም ጉድለት ማጥራትና እሱን ከመውደድና ማላቅ ጋር ለግርማው የሚመጥን በሆነ የተሟላ ምሉዕነት መግለፅ ሲሆን በሰማያትና ምድር መሀል ያለውንም ይሞላል። "ሰላት ብርሃን ነው። " ለአንድ ሰው ለቀልቡም፣ ለፊቱም ፣ በቀብሩም ውስጥ ፣ በትንሳኤ ቀንም ብርሃን ይሆንለታል። "ምፅዋት ማስረጃ ነው።" ምፅዋት የአንድ አማኝ ኢማን እውነተኝነትንና ለምፅዋት የተገባውን ቃልኪዳን ባለማመኑ ምፅዋት ከመስጠት ከሚታቀበው ሙናፊቅ ተቃራኒ መሆኑንም የሚጠቁም ማስረጃ ነው። "ትእግስት (አንፀባራቂ ብርሃን) ወገግታ ነው።" ትእግስት ማለት ነፍስን ከትእግስት ማጣትና መበሳጨት መቆጣጠር ሲሆን ትእግስት እንደ ፀሀይ ብርሀን ሀሩርና ማቃጠል አብሮት የሚኖር ብርሃን ነው። ምክንያቱም መታገስ ነፍስን መታገልና ከዝንባሌዋ ማቀብ የሚፈልግ ስለሆነ አስቸጋሪ ነው። ታጋሽ ሰው ብርሃናማ፣ የተመራና በትክክለኛነት ላይ ዘውታሪ ከመሆን አይወገድም። ትእግስት ሲባል አላህን በመታዘዝ ላይ ፣ አላህን ከመወንጀል በመራቅ ላይ መታገስ እና ከመከራና ከአለማዊ የችግር ዓይነቶች መታገስ ነው። ቁርኣንን በማንበብና ተግባራዊ በማድረግህ ምክንያት "ቁርኣን ላንተ ማስረጃ

ነው።" ወይም በሱ ሳይሰሩና ሳያነቡ ቁርኣንን በመተዉ ምክንያት "በአንተ ላይ ማስረጃ ይሆናል።" ቀጥሎ ነቢዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ሰዎች ሁሉ እንደሚለፉ፣ ለተለያዩ ተግባራትም እንደሚበታተኑ፣ ከእንቅልፋቸው በመንቃት ለተለያዩ ተግባራት ከቤቶቻቸው እንደሚወጡ ተናገሩ። ከነሱም መካከል በአላህ ትእዛዝ ላይ በመፅናት ነፍሱን ከእሳት ነፃ የሚያወጣ ሲኖር ፤ ከነሱም ውስጥ ከዚህ የአላህ ትእዛዝ በመዘንበል ወንጀል ውስጥ የሚወድቅና ነፍሱ እሳት ውስጥ በመግባቷ ለጥፋት የሚዳርጋት አለ።

ጥቅሞች

  • ንፅህና ሁለት አይነት ነው። ውጫዊ ንፅህና በዉዱእ እና በገላ ትጥበት ሲሆን፤ ውስጣዊ ንፅህና ደግሞ በተውሒድ፣ በኢማንና መልካም ስራ የሚመጣ ነው።
  • ሰላት ለአንድ ባሪያ በዱንያም ሆነ በትንሳኤ ቀን ብርሃን ስለሆነ ሰላትን በጥንቃቄ መስገድ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን እንረዳለን።
  • ምፅዋት የእውነተኛ ኢማን ማስረጃ ነው።
  • ቁርኣን በአንተ ላይ ሳይሆን ለአንተ ማስረጃ እንዲሆን ቁርኣንን መተግበር እና ማመን አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን እንረዳለን።
  • ነፍስ በአምልኮ ካልጠመድካት በወንጀል ታጠምድሀለች።
  • ሁሉም ሰው መስራቱ የማይቀር ጉዳይ ነው። ወይ ነፍሱን በአምልኮ ነፃ ያወጣታል ወይም በወንጀል ለጥፋት ይዳርጋታል።
  • ትዕግስት እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ቻይነትንና ምንዳን ከአላህ ማሰብ ይፈልጋል።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

10 አንድ ጊዜ

ትርጉም እና ምንጭ

ከኢብኑ መስዑድ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው: «የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና እንዲህ ብለዋል: "እኔ ወደ ሰማይ ባረግኩበት ምሽት ኢብራሂምን አገኘኋቸው። እንዲህም አሉኝ ‹ሙሐመድ ሆይ! ለኡመትህ ከኔ የሆነን ሰላምታን አቅርብ! ጀነት ምርጥ አፈርና ጣፋጭ ውሃ እንዳላት ጀነት ገላጣ (ዛፍ የሌለባት) ሜዳ እንደሆነችና የሚተከልባትም ሱብሓነላህ ወልሐምዱሊላህ ወላኢላሃ ኢለሏህ ወሏሁ አክበር [በማለት] እንደሆነ ንገራቸው።›"»

ቲርሚዚ ዘግበውታል። ደረጃ: በማመሳከሪያዎቹ ሐሰን ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና በኢስራእና ሚዕራጅ ምሽት የአላህ ፍፁም ወዳጅ የሆኑትን ኢብራሂምን ዐለይሂ ሰላም እንዳገኙ ተናገሩ። ለርሳቸውም «ሙሐመድ ሆይ! ለኡመትክ የኔን ሰላምታ አድርስ! ጀነት አፈሯ ምርጥና ውሃዋም ጨውነት የሌለው ጣፋጭ ውሃ እንደሆነ፤ ጀነት ዛፍ የሌለበት ቀጥ ያለና ሰፊ ሜዳ ሲሆን የጀነት ተክልም ምርጥ ንግግሮችና ቀሪ የሆኑ መልካም ስራዎች እንደሆኑ እነርሱም: "ሱብሓነላህ" "ወልሐምዱሊላህ" "ወላኢላሃ ኢለሏህ" "ወሏሁ አክበር" እንደሆኑና አንድ ሙስሊም በደጋገማቸው ቁጥር ጀነት ውስጥ ተክል እንደሚተከልለት ንገራቸው።» አሉ።

ጥቅሞች

  • የጀነት ተክሎችን ለማብዛት ዚክርን በማዘውተር ላይ መነሳሳቱን እንረዳለን።
  • ይህ ኢስላማዊው ማህበረሰብ የኢብራሂም (ዐለይሂ ሰላም) ሰላምታ ስለተላከላቸው ደረጃቸውን ያስረዳናል።
  • ኢብራሂም (ዐለይሂ ሰላም) የሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ኡመት አላህን ማውሳት እንዲያበዙ ማነሳሳታቸውን እንረዳለን።
  • ጢቢይ እንዲህ ብለዋል: "ጀነት ዛፍ የሌለባት ገላጣ ሜዳ ናት። ከዚያም ግን አላህ በችሮታው በሰሪዎች ስራ ልክ ጀነት ውስጥ ዛፎችንና ህንፃዎችን አስገኘ። ሁሉም ሰሪ በስራው ምክንያት እርሱ የተለየበት ፀጋ አለው። ከዚያም አላህ ሰውዬው ይህን ምንዳ እንዲያገኝ ለተፈጠረለት አላማ ስራውን ካገራለት በኋላ እነዚህ ዛፎችንም እንደሚተክል አደረገው።"

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

11 አንድ ጊዜ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሁረይራ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንዲህ ብለዋል: "ሰዎች አላህን ያላወሱበትና በነቢያቸው ላይ ሶላት ያላወረዱበት መቀማመጥ ከተቀመጡ በነርሱ ላይ ቁጭት ይሆንባቸዋል። ከፈለገ ይቀጣቸዋል ከፈለገም ይምራቸዋል።"

رواه أبو داود والترمذي والنسائي في الكبرى ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አላህን ከማውሳት ከመዘናጋት አስጠነቀቁ። እርሱም ሰዎች አላህን በርሱ ያላወሱበትና በመልክተኛው (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ላይ ሶላት ያላወረዱበት መቀማመጥ ከተቀመጡ ይህ መቀማመጥ የትንሳኤ ቀን በነርሱ ላይ ቁጭት፣ ፀፀት፣ ክስረትና ጉድለት ይሆንባቸዋል። ከፈለገ አላህ በቀደመ ወንጀላቸውና ባለባቸው ጉድለት ምክንያት ይቀጣቸዋል። ከፈለገም በችሮታውና በእዝነቱ ለነርሱ ይምራቸዋል።

ጥቅሞች

  • በዚክር ላይ መነሳሳቱና ትሩፋቱ መገለፁን ተረድተናል።
  • አላህና መልክተኛው (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና የሚወሱበት ቦታ ላይ መቀማመጥ ትሩፋት እንዳለው፤ ይህ የሌለበት መቀማመጥ ደግሞ በሰዎቹ ላይ የትንሳኤ ቀን የእድለቢሶች መቀማመጥ እንደሆነ እንረዳለን።
  • አላህን ከማውሳት ከመዘናጋት የመጣው ክልከላ በመቀማመጥ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። ይልቁንም ሌሎችንም ሁኔታዎች ያጠቃልላል። ነወዊይ እንዲህ ብለዋል: "አንድ ስፍራ ላይ የተቀመጠ ሰው አላህን ከማውሳቱ በፊት ያንን ስፍራ መለየቱ ይጠላል።"
  • የትንሳኤ ቀን የሚያጋጥማቸው ቁጭት ወይ ወቅቱን አላህን በመገዛት ስላልተጠቀሙበት ምንዳና አጅር ስላመለጣቸው ነው፤ ወይም ደግሞ ወቅቱን በወንጀል በማሳለፋቸው ስለተጠመዱ በሚያጋጥማቸው ወንጀልና ቅጣት ነው።
  • መዘናጋቱ የሚፈቀዱ ነገሮች ላይ በመጠመድ ምክንያት ለሆነ ሰው ይህ ማስጠንቀቂያ ከመጣ ሀሜት፣ ሰውና ሰውን ማጣላትንና የመሳሰሉትን ክልክል ነገሮች ባካተተ ስብስቦች ላይ ተጠምዶ የተዛናጋስ ወንጀሉ እንዴት ይሆን?

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

ጥያቄዎች

በዚህ ገጽ ላይ ምን አለ?

በላጩ ዚክር: እያንዳንዳቸው በዐረብኛ፣ ከትርጉማቸው፣ ከመጡበት ሐዲስ፣ ከደረጃቸው እና ከማብራሪያ ጋር።

ትርጉሞቹ ከየት ናቸው?

ከHadeethEnc.com፣ የተተረጎሙ የነቢዩ ሐዲሶች ኢንሳይክሎፒዲያ። እያንዳንዱ ሐዲስ እነሱ እንዳሳተሙት፣ ከምንጩ እና ከደረጃው ጋር እንዲሁም ወደ ዋናው የሚወስድ ማስፈንጠሪያ ይዞ ይቀርባል።

ቆጣሪው እንዴት ይሠራል?

ከዚክሩ ስር ያለውን ቆጣሪ ይንኩ፣ እስከ ዜሮ ወደ ኋላ ይቆጥራል። በዚህ ገጽ ላይ ብቻ ይሠራል፣ ምንም ነገር አይቀመጥም።

የዕለት ማስታወሻ ማግኘት እችላለሁ?

አዎ። ለAndroid የሆነው ነፃው የQabas መተግበሪያ የጠዋት እና የማታ ዚክርን በየቀኑ ያስታውስዎታል፣ ተመሳሳይ ቆጣሪም አለው።