የምሕረት ዱዓ (ኢስቲግፋር)

ሰዪዱል ኢስቲግፋር እና ሌሎች ከሱና የተገኙ ምሕረት የመለመኛ ቃላት።

1 አንድ ጊዜ

اللَّهُمَّ أَنْتَ رَبِّي لَا إِلَهَ إِلَّا أَنْتَ خَلَقْتَنِي وَأَنَا عَبْدُكَ وَأَنَا عَلَى عَهْدِكَ وَوَعْدِكَ مَا اسْتَطَعْتُ أَعُوذُ بِكَ مِنْ شَرِّ مَا صَنَعْتُ أَبُوءُ لَكَ بِنِعْمَتِكَ عَلَيَّ وَأَبُوءُ لَكَ بِذَنْبِي فَاغْفِرْ لِي فَإِنَّهُ لَا يَغْفِرُ الذُّنُوبَ إِلَّا أَنْتَ

ትርጉም እና ምንጭ

ከሸዳድ ቢን አውስ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው: ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ አሉ: "የምህረት አጠያየቅ (የኢስቲግፋር) አለቃ 'አልላሁመ አንተ ረቢ ላ ኢላሃ ኢላ አንተ፣ ኸለቅተኒ ወአነ ዐብዱክ፣ ወአነ ዓላ ዐህዲከ ወወዕዲከ ማስተጦዕቱ፣ አዑዙ ቢከ ሚን ሸሪ ማ ሶነዕቱ፣ አቡኡ ለከ ቢኒዕመቲከ ዐለየ፣ ወአቡኡ ለከ ቢዘንቢ ፈግፊር ሊ፣ ፈኢነሁ ላየግፊሩዝ-ዙኑበ ኢላ አንተ።' ማለትህ ነው።'" እንዲህም ብለዋል "በርሷ አምኖ ቀን ላይ ያላትና በዛው ቀን ከማምሸቱ በፊት የሞተ ሰው እርሱ ከጀነት ባለቤቶች ነው። በርሷ አምኖ ምሽት ላይ ያላትና ከማንጋቱ በፊት የሞተ ሰውም እርሱ ከጀነት ባለቤቶች ነው።" (ትርጉሙም: አላህ ሆይ! አንተ ጌታዬ ነህ፤ ከአንተ በቀር በእውነት የሚመለክ የለም፤ ፈጥረሀኛል እኔም ባሪያህ ነኝ፣ እኔ በቻልኩት መጠን በቃል ኪዳንህ ላይ እገኛለሁ፤ ከሰራሁት ክፋት በአንተ እጠበቃለሁ፣ በኔ ላይ የዋልከውን ፀጋ አረጋግጣለሁ፣ ወንጀሌንም ላንተ አረጋግጣለሁና ማረኝ! እነሆ ካንተ በቀር ወንጀሎችን የሚምር የለምና።)

ቡኻሪ ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ምህረት የሚጠየቅበት የተለያዩ ቃላቶች እንዳሉና በላጩና ትልቁ አንድ ባሪያ እንዲህ ብሎ መጠየቁ እንደሆነ ተናገሩ: "አልላሁመ አንተ ረቢ ላ ኢላሃ ኢላ አንተ፣ ኸለቅተኒ ወአነ ዐብዱክ፣ ወአነ ዓላ ዐህዲከ ወወዕዲከ ማስተጦዕቱ፣ አዑዙ ቢከ ሚን ሸሪ ማ ሶነዕቱ፣ አቡኡ ለከ ቢኒዕመቲከ ዐለየ፣ ወአቡኡ ለከ ቢዘንቢ ፈግፊር ሊ፣ ፈኢነሁ ላየግፊሩዝ-ዙኑበ ኢላ አንተ።" (ትርጉሙም: አላህ ሆይ! አንተ ጌታዬ ነህ፤ ከአንተ በቀር በእውነት የሚመለክ የለም፤ ፈጥረህኛል እኔም ባሪያህ ነኝ፣ እኔ በቻልኩት መጠን በቃል ኪዳንህ ላይ እገኛለሁ፤ ከሰራሁት ክፋት በአንተ እጠበቃለሁ፣ በኔ ላይ የዋልከውን ፀጋ አረጋግጣለሁ፣ ወንጀሌንም ላንተ አረጋግጣለሁና ማረኝ! እነሆ ካንተ በቀር ወንጀሎችን የሚምር የለምና።) በቅድሚያ ባሪያው የአላህን ብቸኝነት ያረጋግጣል። አላህ ፈጣሪው፣ ምንም አጋር ሳይኖረው የሚያመልከው መሆኑን፤ ጥራት ለተገባው አላህ የገባውን በርሱ የማመንና ለርሱ ታዛዥ የመሆንን ቃልኪዳን በአቅሙ ልክ እንደሚወጣ ያረጋግጣል። በአቅሙ ልክ ቃሉን እንደሚወጣ የሚያረጋግጠውም አንድ ባሪያ ምንም ያክል በአምልኮ ላይ ቢቆም አላህ ያዘዘውን ሁሉ መፈፀም ስለማይችል ነው። ለተዋለለት ፀጋ የሚገባውን ምስጋናም ማቅረብ አይችልም። ወደ አላህም ይጠጋል፣ በርሱም ይጠበቃል፣ ባሪያ ከሰራው ክፋት መጠበቂያው አላህ ነውና። አላህ ለርሱ የዋለለትን ፀጋም በታዛዥነት ለርሱ ያረጋግጣል፤ እውቅናንም ይሰጣል። ወደ ነፍሱ በመመለስም ወንጀሉና ኃጢአቱን ያረጋግጣል፤ ያምናልም። በዚህ መልኩ ወደ አላህ ከተቃረበ በኋላ ጌታው እንዲምረው፣ ወንጀሎቹን እንዲሸሽግለት፣ በይቅር ባይነቱ፣ በችሮታውና እዝነቱ ከወንጀሎቹ እንዲጠብቀውም ዱዓ ያደርጋል። ምክንያቱም ከአላህ በቀርም ወንጀሎችን የሚምር የለምና። ቀጥለውም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ይህቺ ዱዓ ከንጋትና ምሽት ውዳሴዎች መካከል መሆኗንና በቀኑ መጀመሪያ ፀሀይ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ ወደ መግቢያዋ ዘንበል እስክትል ድረስ ባለው ወቅት ላይ በእርግጠኝነት፣ መልዕክቷን በማሰብ አምኖባት ካለ በኃላ የሞተ ሰው ጀነት የሚገባ መሆኑን ተናገሩ። በምሽትም ወቅት እርሱም ፀሀይ ከገባችበት አንስቶ ጎህ እስኪወጣ ድረስ ያለ ሰውና ከመንጋቱም በፊት የሞተ ጀነት ይገባል።

ጥቅሞች

  • ምህረትን የመጠየቂያ ቃላቶች የተለያዩ ሲሆኑ ከፊሉም ከከፊሉ ይበላለጣል።
  • አንድ ባሪያ በዚህ ዱዓ አላህን ለመለመን መጓጓት ይገባዋል። ምክንያቱም የምህረት አጠያየቅ (የኢስቲግፋር) አለቃ ነውና።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

2 አንድ ጊዜ

رَبِّ اغْفِرْ لِي خَطِيئَتِي وَجَهْلِي، وَإِسْرَافِي فِي أَمْرِي كُلِّهِ، وَمَا أَنْتَ أَعْلَمُ بِهِ مِنِّي، اللَّهُمَّ اغْفِرْ لِي خَطَايَايَ، وَعَمْدِي وَجَهْلِي وَهَزْلِي، وَكُلُّ ذَلِكَ عِنْدِي، اللَّهُمَّ اغْفِرْ لِي مَا قَدَّمْتُ وَمَا أَخَّرْتُ، وَمَا أَسْرَرْتُ وَمَا أَعْلَنْتُ، أَنْتَ المُقَدِّمُ وَأَنْتَ المُؤَخِّرُ، وَأَنْتَ عَلَى كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሙሳ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና እነዚህን ዱዓዎች ያደርጉ ነበር: "ረቢግፊርሊ ኸጢአቲ፣ ወጀህሊ፣ ወኢስራፊ ፊ አምሪ ኩሊህ፣ ወማ አንተ አዕለሙ ቢሂ ሚኒ፣ አላሁምመግፊርሊ ኸጧያየ፣ ወዓምዲ፣ ወጀህሊ፣ ወሀዝሊ ወኩሉ ዛሊከ ዒንዲ፤ አላሁመግፊርሊ ማ ቀደምቱ፣ ወማ አኸርቱ፣ ወማ አስረርቱ፣ ወማ አዕለንቱ፤ አንተል ሙቀዲሙ፣ ወአንተል ሙአኺሩ፣ ወአንተ ዐላ ኩሊ ሸይኢን ቀዲር" ትርጉሙም "ጌታዬ ሆይ! ወንጀሌን፣ አለማወቄን፣ በሁሉም ነገር ወሰን ማለፌን፣ አንተ ከኔ የበለጠ የምታውቀውንም ማረኝ። አላህ ሆይ! ወንጀሌን፣ ሆን ብዬ የሰራሁትን፣ አለማወቄን፣ ቀልዴን ማረኝ፤ ይህ ሁሉም ከኔው ነው። አላህ ሆይ! ያስቀደምኩትን፣ ያዘገየሁትን፣ የመሰጠርኩትን፣ ግልፅ ያወጣሁትን ወንጀል ማረኝ፤ አንተ አስቀዳሚ ነህ፣ አንተም የሚያዘገይ ነህ፣ አንተም በሁሉም ነገር ላይ ቻይ ነህ።" ማለት ነው።

ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ጠቅላይ ከሆኑት የነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ዱዓዎች መካከል ይህ አንዱ ነበር:

"ጌታዬ ሆይ! ወንጀሌን ማረኝ" ሀጢዐቴን "አለማወቄንም" ያለ እውቀት ከኔ የተከሰተውንም ወንጀል ማረኝ።

"በሁሉም ነገሬ ወሰን ማለፌንም" ከልክ ማለፌንም ማጓደሌንም ማረኝ።

"አንተ ከኔ የበለጠ የምታውቀውንም ማረኝ።" አንተ አውቀኸው እኔ የረሳሁትን ማለት ነው።

"አላህ ሆይ! ወንጀሌንና ሆን ብዬ የሰራሁትን ማረኝ" ወንጀልነቱን አውቄና ሆን ብዬ የሰራሁትንም ማረኝ።

"ምሬንም ቀልዴንም" በቀልድ የሰራሁትንም በሁለቱም ሁኔታ ላይ ሆኜ የሰራሁትንም ማረኝ።

"ይህ ሁሉ ከኔ ነው።" የተጠቀሱት ወንጀሎችና ነውሮች ቢሰበሰቡ ከኔው ናቸው።

"አላህ ሆይ! ያስቀደምኩትን ወንጀል ማረኝ!" ያለፈውን "ያዘገየሁትንም ማረኝ" ለወደፊት የምሰራውን ማረኝ።

"የመሰጠርኩትንም" የደበቅኩትን "ግልፅ ያወጣሁትንም" ይፋ ያወጣሁትን ማረኝ።

"አንተ አስቀዳሚ ነህ! አንተም የሚያዘገይ ነህ!" ከፍጥረትህ የፈለግከውን ወደ እዝነትህ በመግጠምህም ለምትወደው ነገር ታስቀድማለህ። አንተ የፈለግከውንም ሰው እርሱን በማዋረድ ከነዚህ ነገሮች ታዘገየዋለህ። ከነገሮች ያዘገየኸውን የሚየስቀድም፣ ያስቀደምከውንም የሚያዘገይ የለም።

"አንተ በሁሉም ነገር ላይ ቻይ ነህ።" ችሎታው የተሟላ፣ ፍላጎቱ የተሟላ፣ ለምትሻው ነገር ሁሉ ፈፃሚ ነህ ማለት ነው።

ጥቅሞች

  • የዚህ ዱዓ ደረጃና፣ ነቢዩን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና በመከተል በዚህ ዱዓ ላይ መጓጓት እንደሚገባ እንረዳለን።
  • ወሰን ከማለፍ መከልከሉ። ወሰን አላፊ ለቅጣት የተቃረበ ነው።
  • አላህ በሰው ልጅ ላይ ሰው ስለራሱ ከሚያውቀውም የበለጠ አዋቂ በመሆኑ ሁሉም ሰው ሳያውቅ ሊሳሳት ስለሚችል ጉዳዩን ሁሉ ወደ አላህ ማስጠጋት ይገባዋል።
  • የሰው ልጅ በምሩ እንደሚጠየቀው ሁሉ በቀልዱም ይጠየቃል። ስለዚህም በቀልዶቹ ላይ መጠንቀቅ ግዴታው ነው።
  • ኢብኑ ሐጀር አልዐስቀላኒይ እንዲህ ብለዋል: «ይህ ሐዲስ በተዘገበበት ሰነዶች ባጠቃላይ ይህ ዱዓ የሚባልበት የተለየ ቦታ እንዳለው የሚጠቁም አንድም ማስረጃ አላየሁም። የዚህ ዱዓ አብዛኛው ክፍል የሶላት መጨረሻ ላይ እንደሚባል መጥቷል። በለይል ሶላት ውስጥ ይሉት እንደነበርና በተጨማሪ በሶላት መጨረሻ ላይ ይሉትም እንደነበር መጥቷል። የሶላት መጨረሻ ላይ ሲባል ከማሰላመት በፊት ነው ወይስ በኋላ ነው በሚለው ግን ዘገባዎች ተለያይተዋል።»
  • ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ምህረት የሚጠይቁት ወንጀል ሰርተው ነውን? ለመተናነስና ነፍሳቸውን ዝቅ ለማድረግ ብለው ነው፤ ወይም የተሟላ አፈፃፀም ባመለጣቸውና በላጩን አፈፃፀም መተዋቸውን እንደ ወንጀል ቆጥረውት ነው፤ ወይም በመርሳት የሰሩትን ወንጀል ነው፤ ወይም ከነቢይነት በፊት ለሰሩት ወንጀል ነው ያሉ አሉ። ወንጀላቸው እንዲማር በሚል ሳይሆን ያሉት ምህረት መጠየቅ በራሱ መፈፀሙ ግዴታ የሆነ አምልኮ ስለሆነ ነው ያሉም አሉ። ይህን ያሉት ኡመታቸው ምህረትን በመተው ደህንነት እንዳይሰማቸው ኡመታቸውን ለማንቃትና ለማስተማር ብለው ነው ያሉም አሉ።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

3 አንድ ጊዜ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሁረይራ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከላቀውና ከተከበረው ጌታቸው ባስተላለፉት (ሐዲሥ) እንዲህ አሉ "አንድ ባሪያ አንድን ወንጀል ሰራና እንዲህ አለ "አላህ ሆይ! ወንጀሌን ማረኝ! " የጠራውና ከፍ ያለውም እንዲህ አለ "ባሪያዬ ወንጀልን ሰርቶ ወንጀልን የሚምርና በወንጀሉም የሚይዘው ጌታ እንዳለው አወቀ!" ከዚያም ደግሞ ወንጀል ሰራና እንዲህ አለ "ጌታዬ ሆይ! ወንጀሌን ማረኝ!" የጠራውና ከፍ ያለውም እንዲህ አለ "ባሪያዬ ወንጀልን ሰርቶ ወንጀልን የሚምርና በወንጀሉም የሚይዘው ጌታ እንዳለው አወቀ!" ከዚያም አሁንም ደግሞ ወንጀል ሰራና እንዲህ አለ "ጌታዬ ሆይ! ወንጀሌን ማረኝ!" የጠራውና ከፍ ያለውም እንዲህ አለ "ባሪያዬ ወንጀልን ሰርቶ ወንጀልን የሚምርና በወንጀሉም የሚይዘው ጌታ እንዳለው አወቀ! የፈለግከውን ስራ በርግጥ ላንተ ምሬሃለሁ።"

ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከጌታቸው በሚያወሩት ሐዲሥ አንድ ባሪያ አንድ ወንጀል ሰርቶ ከዚያም "አላህ ሆይ! ወንጀሌን ማረኝ!" ካለ አላህ "ባሪያዬ ወንጀልን ሰርቶ ወንጀሉን የሚምረው፣ የሚሸሽገውና ይቅር የሚለው ወይም በወንጀሉ የሚቀጣው ጌታ እንዳለው አወቀ! በርግጥም ምሬዋለሁ" እንደሚል ነገሩን። ከዚያም ባሪያው በድጋሚ ወንጀል ይሰራና "ጌታዬ ወንጀሌን ማረኝ!" ይላል። አላህም "ባሪያዬ ወንጀልን ሰራ። ወንጀሉን የሚምረው፣ የሚሸሽገውና ይቅር የሚለው ወይም በወንጀሉ የሚቀጣው ጌታ እንዳለው አወቀ! በርግጥም ለባሪያዬ ምሬዋለሁ" ይላል። ከዚያም ባሪያው በድጋሚ ወንጀል ይሰራና "ጌታዬ ወንጀሌን ማረኝ!" ይላል። አላህም "ባሪያዬ ወንጀልን ሰርቶ ወንጀሉን የሚምረው፣ የሚሸሽገውና ይቅር የሚለው ወይም በወንጀሉ የሚቀጣው ጌታ እንዳለው አወቀ! በርግጥም ምሬዋለሁ። ወንጀልን በሰራ ቁጥር ወንጀሉን በመተውና በመፀፀት ዳግም ወደ ወንጀል ላለመመለስም ቆርጦ እየወሰነ ነገር ግን ነፍሱ እያሸነፈችው ወንጀል ላይ በድጋሚ እየወደቀ በዚህ መልኩ ወንጀል ቢሰራም ተውበት ማድረግን እስካዘወተረ ድረስ የሰራውን ቢሰራ እምረዋለሁ። ተውበት ያለፈውን ወንጀል ታብሳለችና።" ይላል።

ጥቅሞች

  • አላህ በባሮቹ ላይ ያለው እዝነት ስፋቱን ፤ የሰው ልጅ ምንም ያክል ወንጀል ቢሰራ ወደ አላህ ተውበት ካደረገና ከተመለሰ አላህ ተውበቱን እንደሚቀበለው እንረዳለን።
  • በአላህ ያመነ የጌታውን ይቅርታ ተስፋ ያደርጋል፣ ቁጣውንም ይፈራል፣ ወደ ተውበት ይቻኮላል እንጂ በወንጀል ላይ አይቀጥልም።
  • የትክክለኛ ተውበት መስፈርቶች: ከወንጀል መውጣት፣ በወንጀሉም መፀፀት፣ ዳግም ወደ ወንጀል ላለመመለስ መቁረጥ ነው። ተውበት የሚያደርገው ባሮችን በገንዘብ ወይ በክብር ወይ በነፍስ ከመበደል ወንጀል ከሆነ አራተኛ መስፈርት ይጨመራል። እሱም: ተበዳዩ ባለመብት ሀላል እንዲያደርግለት (ዓውፍ እንዲለው) መጠየቅ ወይም ሓቁን መስጠት ነው።
  • አንድን ባሪያ ስለዲኑ ጉዳይ አዋቂ የሚያደርገው የሆነውን አላህን ማወቅ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ተረድተናል። ስለአላህ ማወቁ ወንጀል በሰራ ቁጥር ተስፋ ሳይቆርጥና ወንጀሉ ላይ ሳይዘልቅ እንዲቶብት ያደርገዋልና።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

4 አንድ ጊዜ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአነስ ቢን ማሊክ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: «የአላህን መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ: "አላህ ተባረከ ወተዓላ እንዲህ ብሏል: ‹የአደም ልጅ ሆይ አንተ እስከለመንከኝና እስከከጀልከኝ ድረስ አንተ ላይ ካለብህ ወንጀልህ ጋርም እምርሃለሁ። (በመማሬም) ምንም አይመስለኝም፤ የአደም ልጅ ሆይ! ወንጀሎችህ የሰማይ ደመና ቢደርሱና ከዚያም ምህረት ብትጠይቀኝ እምርሃለሁ። (በመማሬም) ምንም አይመስለኝም፤ የአደም ልጅ ሆይ! ምድርን ሊሞላ በቀረበ ወንጀል እኔ ጋር ብትመጣ ከዚያም በኔ አንድንም ሳታጋራብኝ ብትገናኘኝ እኔም ምድርን ሊሞላ በቀረበ ምህረት ወዳንተ እመጣለሁ።›"»

ቲርሚዚ ዘግበውታል። ደረጃ: ሐሰን ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና በሐዲሠል ቁድስ ውስጥ አላህ እንዲህ እንዳለ ተናገሩ: የአደም ልጅ ሆይ! እኔን በመለመን፣ እዝነቴን በመከጀልና ተስፋ ባለመቁረጥ ላይ እስከዘወተርክ ድረስ ይህ ወንጀልህና ሀጢዐትህ ከትላልቅ ወንጀሎች ቢሆንም እንኳ እሸሽገዋለሁ፣ ምንም ሳይመስለኝም አብሰዋለሁ። የአደም ልጅ ሆይ! ወንጀልህ በሰማይና በምድር መካከል ያለውን በሚሞላና ምድርንም ከጫፍ እስከጫፍ በሚደርስና ጎኖቿን በሚያጠቃልል መልኩ ቢበዛ ከዚያም ምህረት ብትጠይቀኝ ብዛቱ ምንም ሳይመስለኝ ሁሉንም ላንተ አብሰዋለሁም እምርሃለሁኝም።

የአደም ልጅ ሆይ! አንተ ከሞት በኋላ ወደኔ ምድርን በሚሞላ ወንጀሎችና ሀጢዐቶች ብትመጣ በብቸኝነቴ አምልከኸኝ በኔ አንድንም ሳታጋራ ከሆነ የሞትከው እነዚህን ወንጀሎችህንና ሀጢዐቶችህን ምድርን በሚሞላ ምህረት እገናኛቸዋለሁ። እኔ ምህረተ ሰፊ ነኝና። ከሺርክ በስተቀርም ሁሉንም ወንጀሎችህን እምራለሁ።

ጥቅሞች

  • የአላህ እዝነትና ምህረት ሰፊ መሆኑንና ደረጃውንም እንረዳለን።
  • የተውሒድን ትሩፋት እንረዳለን። አላህ ለተውሒድ ሰዎች ወንጀልና ሀጢዐታቸውን ይምራል።
  • የሺርክን አደጋና አላህ አጋርያንን እንደማይምርም እንረዳለን።
  • ኢብኑ ረጀብ እንዲህ ብለዋል: «ይህ ሐዲሥ ወንጀልን የሚያስምሩትን ሶስት ሰበቦች አጠቃልሏል። የመጀመሪያው: ከመከጀል ጋር ዱዓ ማድረግ ነው። ሁለተኛ: ምህረትን መጠየቅና ንስሀን መፈለግ ነው። ሶስተኛ: በተውሒድ ላይ መሞት ነው።»
  • ይህ ሐዲሥ ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ከጌታቸው ከሚያወሩት ሐዲሥ መካከል አንዱ ነው። "ሐዲሠል ቁድሲይ" ወይም "ሐዲሠል ኢላሂይ" በመባልም ይጠራል። ይህም ማለት ቃሉም መልዕክቱም ከአላህ የሆነና ነገር ግን በማንበቡ እንደማምለክ፣ ለርሱ ዉዱእ ማድረግና የርሱን አምሳያ አምጡ ብሎ አላህ መገዳደሩን የመሰሉ የቁርአን መለዮዎች የሌለው ነው።
  • ወንጀሎች ሶስት አይነቶች ናቸው: የመጀመሪያው: በአላህ ማጋራት ነው። ይህም አላህ የማይምረው ወንጀል ነው። አላህ ዐዘ ወጀል እንዲህ ብሏል {እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ።} ሁለተኛው: አንድ ባሪያ በርሱና በጌታው መካከል ባለው ጉዳይ በወንጀልና ሀጢዐት ነፍሱን መበደሉ ነው። ይህንንም አላህ ከሻ የሚያልፈውና ይቅር የሚለው ነው። ሶስተኛ: አላህ አንዳችም ይቅር የማይለውና የማይተወው ወንጀል ነው። እርሱም: ባሮች አንዳቸው አንዳቸውን መበደላቸው ነው። ይህንንም የግድ የማመሳሰል ፍርድ ተፈፃሚ ይሆንበታል።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

ጥያቄዎች

በዚህ ገጽ ላይ ምን አለ?

የምሕረት ዱዓ: እያንዳንዳቸው በዐረብኛ፣ ከትርጉማቸው፣ ከመጡበት ሐዲስ፣ ከደረጃቸው እና ከማብራሪያ ጋር።

ትርጉሞቹ ከየት ናቸው?

ከHadeethEnc.com፣ የተተረጎሙ የነቢዩ ሐዲሶች ኢንሳይክሎፒዲያ። እያንዳንዱ ሐዲስ እነሱ እንዳሳተሙት፣ ከምንጩ እና ከደረጃው ጋር እንዲሁም ወደ ዋናው የሚወስድ ማስፈንጠሪያ ይዞ ይቀርባል።

የዕለት ማስታወሻ ማግኘት እችላለሁ?

አዎ። ለAndroid የሆነው ነፃው የQabas መተግበሪያ የጠዋት እና የማታ ዚክርን በየቀኑ ያስታውስዎታል፣ ተመሳሳይ ቆጣሪም አለው።