በሶላት ውስጥ ዱዓዎች: መክፈቻ፣ ሩኩዕ፣ ሱጁድ እና ተሸሁድ

ነቢዩ ﷺ በሶላት ውስጥ ከመክፈቻ ተክቢር እስከ ሰላም ያደረጓቸው ዱዓዎች።

1 አንድ ጊዜ

اللهُمَّ بَاعِدْ بَيْنِي وَبَيْنَ خَطَايَايَ كَمَا بَاعَدْتَ بَيْنَ الْمَشْرِقِ وَالْمَغْرِبِ، اللهُمَّ نَقِّنِي مِنْ خَطَايَايَ كَمَا يُنَقَّى الثَّوْبُ الْأَبْيَضُ مِنَ الدَّنَسِ، اللهُمَّ اغْسِلْنِي مِنْ خَطَايَايَ بِالثَّلْجِ وَالْمَاءِ وَالْبَرَدِ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሁረይራ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: «የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ለሶላት ተክቢራ ያደረጉ ጊዜ ከመቅራታቸው በፊት ትንሽ ዝም ይሉ ነበር። እኔም የአላህ መልክተኛ ሆይ! እናትና አባቴ ፊዳ ይሁንሎና በተክቢራ እና በፋቲሓ መካከል ዝምታዎን አይቻለሁና ምንድን ነው የሚሉት? አልኳቸው። እርሳቸውም " 'አልላሁምመ ባዒድ በይኒ ወበይነ ኸጧያየ ከማ ባዐድተ በይነል መሽሪቂ ወልመግሪብ አልላሁምመ ነቂኒ ሚን ኸጧያየ ከማ ዩነቃ አሥሠውቡል አብየዱ ሚነድደነስ፣ አልላሁምመ ኢግሲልኒ ሚን ኸጧያየ ቢሥሠልጂ ወልማኢ ወልበረድ' ነው የምለው" አሉኝ። (ትርጉሙም: አላህ ሆይ! በምስራቅና በምዕራብ መካከል እንዳራራቅከው በኔና በወንጀሌ መካከል አራርቅ! አላህ ሆይ! ነጭ ልብስ ከእድፉ እንደሚጠራው እኔንም ከወንጀሎቼ አጥራኝ! አላህ ሆይ በጤዛ፣ በውሃና በበረዶ ከወንጀሎቼ እጠበኝ። ማለት ነው።)»

ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ለሶላት ተክቢራ ያደረጉ ጊዜ ፋቲሓ ከመቅራታቸው በፊት ትንሽ ዝም ይሉ ነበር። በዚህ ዝም ባሉበት ወቅትም ሶላታቸውን በአንዳንድ ዱዓ ይከፍታሉ። ከነዚህ ከተላለፉልን ዱዓዎች መካከልም: "አልላሁምመ ባዒድ በይኒ ወበይነ ኸጧያየ ከማ ባዐድተ በይነል መሽሪቂ ወልመግሪብ አልላሁመ ነቂኒ ሚን ኸጧያየ ከማ ዩነቃ አሥሠውቡል አብየዱ ሚነደነስ፣ አልላሁመ ኢግሲልኒ ሚን ኸጧያየ ቢሥሠልጂ ወልማኢ ወልበረድ።" ሰውዬው በዚህ ዱዓ በምስራቅና ምዕራብ መካከል ፈፅሞ መገናኘት እንደማይኖረው ሁሉ ከርሱ ጋር በማይገናኙ መልኩ በርሱና በወንጀሎቹ መካከልም አላህ ዐዘ ወጀል እንዲያራርቅ እና ወንጀል ላይ እንዳይወድቅ፤ ወንጀል ላይ ከወደቀ እንኳ ነጭ ልብስ ከእድፍ እንደሚጠራው ከወንጀሉ እንዲያጠራውና እንዲያስወግድለት፣ ከወንጀሉ እንዲያጥበውና የወንጀሉን ሀሩርና ወላፈንንም በውሃ፣ በጤዛና በረዶ እንዲያቀዘቅዝለት ነው ዱዓ የሚያደርገው።

ጥቅሞች

  • ሶላቱ ጮክ ተብሎ የሚቀራበት ቢሆን እንኳ ዱዓንና የሶላት መክፈቻን ዝግ አድርጎ ማድረግ እንደሚገባ እንረዳለን።
  • ሶሐቦች (ረዲየሏሁ ዐንሁም) አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና መልክተኛው (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በእንቅስቃሴም ይሁን እርጋታ ላይ ያላቸውን ሁኔታ ለማወቅ የሚያደርጉትን ጥረት እንረዳለን።
  • ሌሎችም የመክፈቻ ዱዓዎች መጥተዋል። በላጩ ሰውዬው ከነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) የመጡትንና የፀኑትን የመክፈቻ ዱዓዎች በመከተልና በመሸምደድ አንዳንዴ ይሄንን አንዳንዴ ደግሞ ሌሎቹን እየቀያየረ ቢል ነው።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

2 አንድ ጊዜ

سَمِعَ اللهُ لِمَنْ حَمِدَهُ، اللَّهُمَّ رَبَّنَا لَكَ الْحَمْدُ، مِلْءَ السَّمَاوَاتِ وَمِلْءَ الْأَرْضِ وَمِلْءَ مَا شِئْتَ مِنْ شَيْءٍ بَعْدُ

ትርጉም እና ምንጭ

ከኢብኑ አቢ አውፋ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ከሩኩዕ ወገባቸውን ቀና ያደረጉ ጊዜ "ሰሚዐሏሁ ሊመን ሐሚደህ አላሁመ ረበና ለከል ሐምዱ ሚልአስ-ሰማዋቲ ወልአርድ ወሚልአ ማ ሺእተ ሚን ሸይኢን በዕዱ" ይሉ ነበር። ትርጉሙም "አላህ ላመሰገነው ሰው ሰሚ ነው። አላህ ሆይ! ሰማያትን የሞላ፣ ምድርን የሞላ፣ ከነዚህም በኋላ ያሉ የፈለግከውን ነገሮችን የሞላ ምስጋና ላንተ የተገባ ነው።"

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሶላት ውስጥ ከሩኩዕ ወገባቸውን ቀና ያደረጉ ጊዜ "ሰሚዐሏሁ ሊመን ሐሚደህ" ይሉ ነበር። አላህን ያመሰገነ ሰው አላህ ይቀበለዋል፤ ምስጋናውን ተቀብሎ ይመነዳዋል ማለት ነው። ከዚያም "አላሁመ ረበና ለከል ሐምዱ ሚልአስ-ሰማዋቲ ወልአርድ ወሚልአ ማ ሺእተ ሚን ሸይኢን በዕዱ" በሚለው ንግግራቸው ሰማያትን፣ ምድሮችን፣ በመካከላቸው ያለውን፣ አላህ የሻውን ነገርንም ሁሉ በሚሞላ ምስጋና አላህን ያመሰግኑ ነበር።

ጥቅሞች

  • ሰጋጅ የሆነ ሰው ራሱን ከሩኩዕ ቀና ያደረገ ጊዜ ማለቱ የሚወደድለት ዚክር መገለፁ።
  • ከሩኩዕ ከተነሳ በኋላ መረጋጋትና ቀጥ ማለት መደንገጉን እንረዳለን። ምክንያቱም ይህን ዚክር ቀጥ ብሎና ተረጋግቶ ካልሆነ በቀር ማለቱ አይመችምና።
  • በሁሉም ሶላቶች ግዴታም ሆነ ሱና ሶላት ይህንኑ ዚክር ማለቱ የተደነገገ መሆኑን እንረዳለን።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

3 አንድ ጊዜ

اللَّهمَّ اغْفِرْ لي، وارْحَمْنِي، وعافِني، واهْدِني، وارزقْنِي

ትርጉም እና ምንጭ

ከኢብኑ ዐባስ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው: ነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በሁለቱ ሱጁዶች መካከል "አላሁመግፊር ሊ ወርሐምኒ ወዓፊኒ ወህዲኒ ወርዙቅኒ" ይሉ ነበር። ትርጉሙም (አላህ ሆይ! ማረኝ፣ እዘንልኝም፣ ጤናን ለግሰኝም፣ ምራኝም፣ ሲሳይን ለግሰኝም) ማለት ነው።

አቡዳውድ፣ ቲርሚዚ፣ ኢብኑማጀህና አሕመድ ዘግበውታል። ደረጃ: በማመሳከሪያዎቹ ሐሰን ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በሶላታቸው ውስጥ በሁለቱ ሱጁዶች መካከል ሙስሊም የሆነ ሰው በእጅጉ የሚፈልጋቸው ጉዳዮችንና የዱንያንም ሆነ የአኺራን መልካም የሰበሰቡ የሆኑትን: ምህረትን፤ የወንጀል መሸሸግን፤ ይቅር መባልን መፈለግ፤ እዝነቱ እንዲያዳርሰው መፈለግ ፤ ከሚያምታታ፣ ዝንባሌው ከሚገፋፋውና ከበሽታዎችም ጤናማ መሆንን መፈለግ ፤ አላህን ለእውነትና በርሱ ላይ በመፅናት ላይ እንዲመራው መጠየቅ፤ የኢማን፣ የእውቀት ፣ የመልካም ስራ፣ ምርጥና ሐላል የገንዘብ ሲሳይ እንዲለግሰው መለመንን ሁሉ ያጠቃለሉ የሆኑትን እነዚህ አምስት ዱዓዎችን ይለምኑ ነበር።

ጥቅሞች

  • በሁለቱ ሱጁዶች መካከል በምንቀመጥ ወቅት ይህ ዱዓእ መደንገጉን እንረዳለን።
  • ይህ ዱዓእ የዱንያንም ሆነ የአኺራን መልካም ነገሮች ስለጠቀለለ የዚህ ዱዓን ትሩፋትንም እንረዳለን።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

4 አንድ ጊዜ

اللهُمَّ اغْفِرْ لِي ذَنْبِي كُلَّهُ دِقَّهُ، وَجِلَّهُ، وَأَوَّلَهُ وَآخِرَهُ وَعَلَانِيَتَهُ وَسِرَّهُ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሁረይራ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው: «የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሱጁድ ውስጥ እንዲህ ይሉ ነበር "አላሁመግፊርሊ ዘንቢ ኩለሁ ዲቀሁ ወጂለሁ፣ ወአወለሁ ወአኺረሁ፣ ወዐላኒየተሁ ወሲረሁ"» ትርጉሙም "አላህ ሆይ! ደቂቁንም ትልቁንም፣ የመጀመሪያውንም የመጨረሻውንም፣ ግልፁንም፣ ድብቁንም ወንጀሌን ሁሉንም ማረኝ።"

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በሱጁዳቸው ወቅት እንዲህ እያሉ ዱዓእ ያደርጉ ነበር: "አላህ ሆይ ወንጀሌን ማረኝ" በመሸሸጊያህ ሸሽገኝ፤ ተከትሎት የሚመጣውን መከራንም ጠብቀኝ፤ ይቅር በለኝ፤ እለፈኝ (ሁሉንም) ማለትም (ደቂቁንም) ትንሹንም ጥቃቅኑንም፤ (ትልቁንም) ግዙፉንም ብዙውንም፤ (የመጀመሪያውንም) የመጀመሪያውን ወንጀሌንም፤ (የመጨረሻውንም) በነርሱ መካከል ያለውን ወንጀሌንም (ግልፁንም ድብቁንም) ከአንተ በቀር ማንም የማያውቀውን ወንጀሌንም ማረኝ።

ጥቅሞች

  • ኢብኑል ቀይዪም እንዲህ ብለዋል "ትናንሽንም፣ ትላልቅንም፣ ደቂቁንም፣ ግዙፉንም፣ የመጀመሪያውንም፣ የመጨረሻውንም፣ ድብቁንም፣ ግልፁንም ወንጀሎች ብሎ በዚህ በሚጠቀልልና በሚሰበስብ መልኩ ምህረት እንዲያገኝ መለመን ባሪያው ላወቀውም ሆነ ላላወቀው ወንጀሉ ሁሉ ተውበት እንዲያደርግ ነው።"
  • (ደቂቁንም) የሚለውን (ትልቁንም) ከሚለው ያስቀደሙት ጠያቂው ጥያቄውን ቀስ በቀስ እንዲወጣና እንዲያሳድግ ነው። ሌላው ምክንያትም ብዙ ጊዜ ትላልቅ ወንጀሎች የሚከሰቱት በትናንሽ ወንጀሎች ላይ በመዘውተርና ትኩረት ባለመስጠት ነው። ትናንሽ ወንጀሎች ወደ ትላልቅ ወንጀሎች ያደርሳሉ። ወደ አንድ ነገር የሚያደርሱ ነገሮች ደግሞ በማፅደቅም ይሁን በማስወገድ ረገድ መቀደማቸው የተገባ ነው።
  • ከትናንሹም ከትላልቁም ከሁሉም ወንጀሎች ምህረትን በመፈለግ ወደ አላህ መዋደቅ ተገቢ ነው።
  • ነወዊይ እንዲህ ብለዋል: "ይህ ሐዲሥ ዱዓ ስናደርግ ማጠንከርና አንዱ ቃል ከአንዱ ቃል ቢያብቃቃን እንኳ ቃላቶችን ማብዛት እንደሚገባ ያስረዳናል።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

5 አንድ ጊዜ

اللهُمَّ أَعُوذُ بِرِضَاكَ مِنْ سَخَطِكَ، وَبِمُعَافَاتِكَ مِنْ عُقُوبَتِكَ، وَأَعُوذُ بِكَ مِنْكَ لَا أُحْصِي ثَنَاءً عَلَيْكَ أَنْتَ كَمَا أَثْنَيْتَ عَلَى نَفْسِكَ

ትርጉም እና ምንጭ

ከእናታችን ዓኢሻ (ረዲየሏሁ ዐንሃ) -አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና- እንደተላለፈው እንዲህ ብላለች፦ «በአንድ ምሽት የአላህን መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ከፍራሼ ላይ አጣኋቸው። በዳሰሳ ስፈልጋቸውም እጄ መስገጃቸው ላይ የተተከለችው የእግራቸው ውስጥ ላይ አረፈች። እርሳቸውም እንዲህ እያሉ ነበር " አላሁመ አዑዙ ቢሪዷከ ሚን ሰኸጢክ፣ ወቢሙዓፋቲከ ሚን ዑቁበቲክ፣ ወአዑዙ ቢከ ሚንክ፣ ላኡሕሲ ሠናአን ዐለይክ አንተ ከማ አሥነይተ ዐላ ነፍሲክ"» ትርጉሙም "አላህ ሆይ! ከቁጣህ በውዴታህ፣ ከቅጣትህ በይቅር ባይነትህ እጠበቃለሁ፤ ከአንተ በአንተ እጠበቃለሁ፤ አንተ እራስህን ያወደስከውን ያህል ላወድስህ አልችልም።" ማለት ነው።

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ዓኢሻ (ረዲየሏሁ ዐንሃ) -አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና- እንዲህ አለች "ከነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ጎን ተኝቼ ነበር። ሌሊት ላይ አጣኋቸሁ። ቤት ውስጥ ይሰግዱበት የነበረውን ስፍራ በእጄ ዳሰስኩ። በዛን ጊዜም ሱጁድ ላይ ተደፍተው እግራቸውን ተተክለው አገኘሁ። እርሳቸውም እንዲህ እያሉ ነበር:

(በውዴታህ) በኔ ላይም ይሁን በኡመቴ ላይ ከምትቆጣው (ቁጣህ) (እጠበቃለሁ) እቃረባለሁ። (ከቅጣትህ) ይቅር ባይነትህ ብዙ ነውና (በይቅር ባይነትህ) (እጠበቃለሁ)። (በአንተ ከአንተ እጠበቃለሁ።) ውብ በሆኑት ባህሪያትህ የልቅና መገለጫ ከሆኑት ባህሪያትህ እጠበቃለሁ። ከአንተ በቀር ከአንተ ለሚመጣው ቅጣት የሚጠብቅ የለምና። ወደ አላህ በመጠጋት ካልሆነ በቀርም ከአላህ መዳኛም መጠጊያም የለም። (በአንተ ላይ አወድሼ አልዘልቅም።) ፀጋህንና በጎ ውለታህን ቆጥሬ መዝለቅ ስለማልችል አንተ የሚገባህንም ውዳሴ በቁጥርም በገደብም ማወደሱን ብጥር እንኳ አልችልም። ለራስህ የሚገባውን በቂ ውዳሴ በራስህ ላይ ያወደስከው አንተ ብቻ ነህና (አንተ ነፍስህን ባወደስክበት ልክ ማወደስ አልችልም።) አንተን የማወደስ ሐቁን በአግባቡ መወጣት የሚችልስ ሌላ አካል ማን አለና?!

ጥቅሞች

  • ሱጁድ ላይ ይሄን ዱዓ ማለት ተወዳጅ እንደሆነ እንረዳለን።
  • ሚረክ እንዲህ ብለዋል: «በአንድ የነሳኢ ዘገባ ደሞ ይህን ዱዓ ሶላታቸውን አጠናቀው ወደ መኝታቸው ሲወጡ እንደሚሉት ተዘግቧል።»
  • አላህን በቁርአንና ሐዲሥ በመጡ ባህርያቱ ማወደስና በስሞቹ ዱዓ ማድረግ እንደሚወደድ እንረዳለን።
  • ይህ ሐዲሥ ፈጣሪን ሩኩዕና ሱጁድ ውስጥ ማላቅ እንደሚገባ ያስረዳናል።
  • በአላህ ሱብሓነሁ ወተዓላ ዛት መጠበቅ እንደሚፈቀደው በአላህ ባህሪም መጠበቅ እንደሚፈቀድ እንረዳለን።
  • ኸጧቢይ እንዲህ ብለዋል: "ይህ ንግግር ውስጥ ረቂቅ ሀሳብ ይገኛል። እርሱም: እርሳቸው ከአላህ ቁጣ በውዴታው፣ ከቅጣቱ ደሞ በይቅርታው ተጠበቁ። ውዴታና ቁጣ ሁለት ተቃራኒ ነገሮች ናቸው። እንዲሁም ይቅር ባይነትና በወንጀል መቅጣትም ተቃራኒ ናቸው። ለርሱ ተነፃፃሪ የሌለውን አላህን ሱብሓነሁ ወተዓላ ሲጠቅሱ ግን ከርሱ በሌላ ሳይሆን በራሱ ተጠበቁ። የዚህም ሀሳብ: ይቅር ባይነቱ የተጠየቀው አላህ ሊመለክና ሊወደስበት ከሚገባው መብቱ ስለማጓደላችን ነው። (በአንተ ላይ አወድሼ አልዘልቅም።) ሲሉ አንተን በሚገባህ ልክ ማወደስ የምችልበት አቅሙ የለኝም ማለታቸው ነው።"

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

6 አንድ ጊዜ

اللَّهُمَّ صَلِّ عَلَى مُحَمَّدٍ وَعَلَى آلِ مُحَمَّدٍ، كَمَا صَلَّيْتَ عَلَى آلِ إِبْرَاهِيمَ، إِنَّكَ حَمِيدٌ مَجِيدٌ، اللَّهُمَّ بَارِكْ عَلَى مُحَمَّدٍ وَعَلَى آلِ مُحَمَّدٍ، كَمَا بَارَكْتَ عَلَى آلِ إِبْرَاهِيمَ، إِنَّكَ حَمِيدٌ مَجِيدٌ

ትርጉም እና ምንጭ

ከዐብዱረሕማን ቢን አቢ ለይላ እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: "ከዕብ ቢን ዑጅራህ አገኘኝና እንዲህ አለኝ: 'ስጦታ ላበርክትልህን? ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ወደኛ መጡ። እኛም እንዲህ ብለን ጠየቅናቸው የአላህ መልክተኛ ሆይ! በርሶ ላይ እንዴት ሰላምታ እንደምናቀርብ አውቀናል። በርሶ ላይ ሶላት የምናወርደውስ እንዴት ነው? እርሳቸውም፦ ‹አልላሁመ ሶሊ ዐላ ሙሐመዲን ወዐላ ኣሊ ሙሐመዲን ከማ ሶለይተ ዓላ አሊ ኢብራሂመ ኢነከ ሐሚዱን መጂድ፤ አልላሁመ ባሪክ ዓላ ሙሐመዲን ወዓላ አሊ ሙሐመዲን ከማ ባረክተ ዓላ አሊ ኢብራሂመ ኢነከ ሐሚዱን መጂድ። በሉ› አሉን።'" (ትርጉሙም: አላህ ሆይ! ውዳሴህን ለኢብራሂምና ለቤተሰቦቻቸው እንዳወረድክላቸው ሁሉ ለሙሐመድና ለቤተሰቦቻቸው አውርድላቸው፤ አንተ ምስጉንና ኋያል (የላቅክ) ነህና፡፡አላህ ሆይ! ለኢብራሂምና ለቤተሰቦቻቸው ረድዔትን እንዳወረድክላቸው ሁሉ ለሙሐመድና ለቤተሰቦቻቸውም ረድዔትን አውርድላቸው፡፡ አንተ ምስጉንና ኋያል (የላቅክ) ነህና፡፡”)

ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ሶሐቦች አትተሒያቱ ላይ "አስሰላሙ ዐለይከ አይዩሀ ነቢዩ ወረሕመቱሏሂ ወበረካቱሁ… " በማለት በነቢዩ ላይ እንዴት ሰላምታ እንደሚቀርብ ካወቁ በኋላ ነቢዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በርሳቸው ላይ ሶላት እንዴት እንደሚደረግ ጠየቁ። ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በርሳቸው ላይ እንዴት ሶላት እንደሚያወርዱ ነገሯቸው። ትርጉሙም: "አልላሁመ ሶሊ ዐላ ሙሐመዲን ወዓላ አሊ ሙሐመድ" ማለትም: አላህ ሆይ! በላይኛው አለም፤ በርሳቸው፣ እምነታቸውን በተከተሉና አማኝ በሆኑ ቅርብ ዘመዶቻቸውም ላይ በመልካም ትውስታ አወድሳቸው። "ከማ ሶለይተ ዓላ አሊ ኢብራሂም" በኢብራሂም (ዐለይሂ ሰላም) የአላህ ሰላም ይስፈንባቸውና ቤተሰቦች ‐ እነሱም ኢብራሂም፣ ኢስማዒል፣ ኢስሐቅ፣ ዝርያዎቻቸውና አማኝ ተከታዮቻቸው ‐ ላይ ችሮታህን እንደዋልከው በሙሐመድ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ላይም ችሮታህን ዋል። "ኢንነከ ሐሚዱን መጂድ" ማለትም: በዛትህ፣ በባህሪትህ እና በድርጊቶችህ ምስጉን የሆንክ፤ በልቅናህ፣ በስልጣንህና በስጦታህ ሰፊ የሆንክ አንተው ነህ ማለት ነው። "አልላሁመ ባሪክ ዐላ ሙሐመዲን ወዓላ አሊ መሐመድ ከማ ባረክተ ዓላ አሊ ኢብራሂም" ማለትም ለነቢዩ ከመልካሙና ከክብር የላቀውን ስጣቸው፣ ጨምርላቸውም፣ አፅናላቸውም።

ጥቅሞች

  • ቀደምት አበው እውቀታዊ ቁምነገሮችን እንደ ስጦታ ይሰጣጡ እንደነበር እንረዳለን።
  • ሶላት ላይ በመጨረሻው ተሸሁድ ወቅት በነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ላይ ሶላት ማውረድ ግዴታ መሆኑን እንረዳለን።
  • ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ባልደረቦቻቸውን በርሳቸው ላይ እንዴት ሶላትና ሰላም እንደሚያወርዱ ማስተማራቸውን እንረዳለን።
  • ይህ የሶለዋት ይዘት በነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ላይ የተሟላው የሶለዋት ይዘት ነው።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

7 አንድ ጊዜ

اللَّهُمَّ إِنِّي أَعُوذُ بِكَ مِنْ عَذَابِ القَبْرِ، وَمِنْ عَذَابِ النَّارِ، وَمِنْ فِتْنَةِ المَحْيَا وَالمَمَاتِ، وَمِنْ فِتْنَةِ المَسِيحِ الدَّجَّالِ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሁረይራ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ ብለዋል፦ "የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና): 'አሏሁመ ኢኒ አዑዙ ቢከ ሚን ዓዛቢል ቀብሪ ወሚን ዓዛቢ‐ን‐ናር ወሚን ፊትነቲል መሕያ ወል መማት ወሚን ፊትነቲል መሲሒ‐ድ‐ደጃል' እያሉ ዱዓእ ያደርጉ ነበር።" 'ትርጉሙም: አላህ ሆይ! እኔ ከቀብር ቅጣት፣ ከእሳት ቅጣት፣ ከህይወትና ሞት ፈተና እና ከመሲሕ ደጃል ፈተና ባንተው እጠበቃለሁ።' ማለት ነው። በሙስሊም ዘገባ ደግሞ 'አንዳችሁ ከመጨረሻው ተሸሁድ ያጠናቀቀ ጊዜ ከአራት ነገሮች በአላህ ይጠበቅ: ከጀሀነም ቅጣት፣ ከቀብር ቅጣት፣ ከህይወትና ሞት ፈተናና ከመሲሕ ደጃል ክፋት።'ብለዋል።"

ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ከመጨረሻው ተሸሁድ በኋላ ከሶላት ከማሰላመታቸው በፊት ከአራት ነገሮች በአላህ ይጠበቁ ነበር። እኛንም በአላህ ከነርሱ እንድንጠበቅ አዘዙን።

የመጀመሪያው: ከቀብር ቅጣት ነው።

ሁለተኛው: የትንሳኤ ቀን ከእሳት ቅጣት ነው።

ሶስተኛው: ከህይወት ፈተናዎች ሲባል ክልክል ከሆኑ ዓለማዊ ዝንባሌዎችና አጥማሚ ማደናገሪያዎች፤ እንዲሁም በሞት ሰአት ከሚያጋጥሙ ፈተናዎች ሲባል ደግሞ በጣእረ ሞት ሰአት ከኢስላም ወይም ሱና መጥመምን የመሰሉ ወይም በሁለቱ መላእክት መጠየቅን ከመሰለ የቀብር ፈተና ማለት ነው።

አራተኛ: በመጨረሻ ዘመን የሚወጣ ከሆነው ከመሲሕ ደጃል ፈተና ነው። አላህ በርሱ አማካኝነት ባሮቹን ይፈትናል። ዱዓው ላይ እርሱ ተለይቶ የተጠቀሰው የርሱ ፈተናና ማጥመሙ ከባድ ስለሆነ ነው።

ጥቅሞች

  • ይህ መጠበቂያ ዱዓ ከዱንያና ከመጨረሻው ዓለም ክፋቶች መጠበቅን ከሰበሰበ አንገብጋቢና ጠቅላይ ከሆነ ዱዓዎች መካከል አንዱ ነው።
  • የቀብር ቅጣት የተረጋገጠና እውነት መሆኑን እንረዳለን።
  • የፈተናን አደገኝነት እና ከፈተና ለመዳን በአላህ መታገዝና ዱዓ ማድረግ እንደሚገባ እንረዳለን።
  • የደጃል መውጣት የተረጋገጠ መሆኑንና ፈተናው ከባድ መሆኑን እንረዳለን።
  • ከመጨረሻው ተሸሁድ በኋላ ይህን ዱዓ ማለት እንደሚወደድ እንረዳለን።
  • ከመልካም ስራ በኋላ ዱዓ ማድረግ እንደሚወደድ እንረዳለን።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

8 አንድ ጊዜ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሁረይራ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል: "አንድ ባሪያ ወደ ጌታው እጅግ ቅርብ የሚሆነው ሱጁድ ላይ ሳለ ነው። (ስለዚህም) ዱዓእን አብዙ!"

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አንድ ባሪያ ወደ ጌታው እጅግ ቅርብ የሚሆነው ሱጁድ ላይ ሳለ መሆኑን ገለፁ። ይህም ሰጋጅ ከሰውነቱ የላቀና የተከበረው አካሉን ለአላህ በሱጁድ ለመዋደቅ፣ ለመዋረድና ለመተናነስ ሲል መሬት ላይ የሚደፋ በመሆኑ ነው።

ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በሱጁድ ውስጥ ዱዓእ እንድናበዛም አዘዙን። በዚህም ንግግራዊም ድርጊታዊም መተናነስ ይሰባሰባሉ።

ጥቅሞች

  • አምልኮ ባሪያውን ወደ አላህ መቃረብን ትጨምርለታለች።
  • ሱጁድ ዱዓእ ተቀባይነት ከሚያገኝበት ስፍራዎች መካከል አንዱ ስለሆነ ሱጁድ ውስጥ ዱዓእ ማብዛት እንደሚወደድ ተረድተናል።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

ጥያቄዎች

በዚህ ገጽ ላይ ምን አለ?

በሶላት ውስጥ ዱዓዎች: እያንዳንዳቸው በዐረብኛ፣ ከትርጉማቸው፣ ከመጡበት ሐዲስ፣ ከደረጃቸው እና ከማብራሪያ ጋር።

ትርጉሞቹ ከየት ናቸው?

ከHadeethEnc.com፣ የተተረጎሙ የነቢዩ ሐዲሶች ኢንሳይክሎፒዲያ። እያንዳንዱ ሐዲስ እነሱ እንዳሳተሙት፣ ከምንጩ እና ከደረጃው ጋር እንዲሁም ወደ ዋናው የሚወስድ ማስፈንጠሪያ ይዞ ይቀርባል።

የዕለት ማስታወሻ ማግኘት እችላለሁ?

አዎ። ለAndroid የሆነው ነፃው የQabas መተግበሪያ የጠዋት እና የማታ ዚክርን በየቀኑ ያስታውስዎታል፣ ተመሳሳይ ቆጣሪም አለው።