ከምግብ በፊት የሚባል ዱዓ (ቢስሚላህ)

ከምግብ በፊት ምን እንደሚባል እና በምግብ ላይ የአላህ ስም ለምን እንደሚወሳ።

1 አንድ ጊዜ

بِسْمِ اللَّهِ

ትርጉም እና ምንጭ

ከዑመር ቢን አቢ ሰለማህ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: "በአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ጎጆ ውስጥ የምኖር ህፃን ልጅ ነበርኩ። በማዕዱ ላይም እጄ ትሽከረከር ነበር። የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ለኔ እንዲህ አሉኝ ' አንተ ልጅ ሆይ! ቢስሚላህ በል! በቀኝህ ብላ፣ ፊትህ ካለውም ብላ!' ከዚያን ጊዜ በኋላ ከዚህ የአበላል ስርአት አልተወገድኩም።"

ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ዑመር ቢን አቢ ሰለማህ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና የነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ባለቤት የሆነችው የኡሙ ሰለማህ ልጅ ነው። ያደገውም በሳቸው እነፃና እንክብካቤ ስር ነበር። በሚበላበት ወቅት ምግብ ለማንሳት እጁን በእቃው ዙሪያ ያዘዋውር ነበር። ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሶስት የአመጋገብ ስርአቶችን አስተማሩት:

የመጀመሪያው: መብላት ሲጀምር "ቢስሚላሂ" ማለት ነው።

ሁለተኛው: በቀኝ መብላት ነው።

ሶስተኛው: ለርሱ ቅርብ በሆነ ምግብ በኩል መመገብ ነው።

ጥቅሞች

  • ከመብላትና መጠጣት ስርአቶች መካከል መጀመሪያ ቢስሚላህ ማለት አንዱ ነው።
  • ህፃናትን ስርአት ማስተማር እንደሚገባ በተለይ በሰውዬው ሀላፊነት ስር ያለን ልጅ ስርአት ማስተማር እንደሚገባ እንረዳለን።
  • ህፃናትን በማስተማርና ስርአት በማስያዙ ረገድ የነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እዝነትና ልበ ሰፊነትን እንረዳለን።
  • ከፊቱ ካለው መመገብ ከአመጋገብ ስርአቶች መካከል አንዱ ነው። የምግብ አይነቶቹ ብዙ የሆኑ ጊዜ ግን ከፊቱ ውጪ ካለ መውሰድም ይችላል።
  • ሶሐቦች ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ያስተማሯቸውን ስርአት አጥብቀው መያዛቸውን እንረዳለን። ይህንንም ነጥብ "ከዛን ጊዜ በኋላ ከዚህ የአበላል ስርአት አልተወገድኩም።" ከሚለው የዑመር ንግግር እንረዳለን።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

2 አንድ ጊዜ

ትርጉም እና ምንጭ

ከወሕሺይ ቢን ሐርብ -አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው: «እነርሱ "የአላህ መልክተኛ ሆይ! እኛ እየበላን አንጠግብም።" አሏቸው። እርሳቸውም "ምናልባት ተበታትናችሁ ለየብቻ እየበላችሁ ይሆን?" ብለው ጠየቋቸው። እነርሱም "አዎን" አሉ። እርሳቸውም "ምግብ ስትበሉ ተሰብሰቡ። (አንድ ላይ ብሉ) የአላህንም ስም በምግባቹ ላይ አውሱ። አላህ ምግባችሁን ይባርክላችኋል።"»

አቡዳውድ፣ ኢብኑ ማጀህና አሕመድ ዘግበውታል። ደረጃ: ሐሰን ነው።

ማብራሪያ

የተወሰኑ ሶሓቦች ነቢዩን - የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና - እንዲህ በማለት ጠየቁ: "እኛ እንበላለን። ነገር ግን አንጠግብም።"

ነቢዩም - የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና - ለነርሱ እንዲህ አሏቸው: "ምን አልባት ስትበሉ ተበታትናችሁ ለየብቻ ነው እንዴ የምትበሉት?" እነርሱም: "አዎን" አሉ። እርሳቸውም: "ተሰብሰቡ ሳትበታተኑ ብሉ። ስትበሉ ቢስሚላህ በማለት የአላህን ስም አውሱ። በዛም ይባረክላችኋልም ትጠግባላችሁም።" አሏቸው።

ጥቅሞች

  • አብሮ ተሰባስቦ መብላትና ሲበሉ ቢስሚላህ ማለት ምግቡ በረከት እንዲኖረውና ለመጥገብ ምክንያት ናቸው።
  • መበታተን ባጠቃላይ መጥፎ ሲሆን መሰባሰብ በጠቃላይ ደግሞ መልካም ነው።
  • በመሰባሰብ ላይና ሲበሉ ቢስሚላህ በማለት ላይ መነሳሳቱን እንመለከታለን።
  • ሲንዲይ እንዲህ ብለዋል: "በመሰባሰብ ቀለቦች ላይ በረከት ይወርዳል። የአላህን ስም በማውሳት ደግሞ የሸይጧንን ወደ ምግቡ መድረስ ያቅባል።"

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

3 አንድ ጊዜ

ትርጉም እና ምንጭ

ከሑዘይፋ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: «ከነቢዩ - የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - ጋር ማዕድ ለመጋራት የተገኘን ጊዜ የአላህ መልክተኛ - የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - እጃቸውን ወደ ማዕዱ ከመስደዳቸውና (ከመጀመራቸው) በፊት እኛ እጃችንን አንሰድም ነበር። አንድ ቀን ከርሳቸው ጋር ማዕድ ለመጋራት ተገኘን። (ከፍጥነቷ የተነሳ) ልክ እየተገፈተረች በሚመስል መልኩ የሆነች አንዲት ልጅ መጣችና እጇን ወደ ማዕዱ ሰደደች። የአላህ መልክተኛም - የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - እጇን ያዟት። ቀጥሎም (ከፍጥነቱ የተነሳ) ልክ እየተገፈተረ በሚመስል መልኩ አንድ የገጠር ሰውዬ መጣና እጁን ወደ ማዕዱ ሰደደ። የአላህ መልክተኛም - የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - እሱንም እጁን ያዙትና እንዲህ አሉ: "ሸይጧን የአላህ ስም እንዳይወሳበት በማድረግ ምግቡን ለራሱ የተመቸ ያደርገዋል። እርሱም ይህቺን ሴትዮ ምግቡን ለራሱ ለማስመቸት ይዞ መጣ። እጇንም ያዝኳት። ይህንንም ሰውዬ ምግቡን ለራሱ ለማስመቸት ይዞ መጣ። እጁንም ያዝኩት። ነፍሴ በእጁ በሆነው ጌታ እምላለሁ! የሸይጧንን እጅ ከሴትዮዋ እጅ ጋር ይዤዋለሁ።"»

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ሑዘይፋ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንዳወሱት: ከነቢዩ - የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - ጋር ማዕድ ለመጋራት በተገኙ ጊዜ የአላህ መልክተኛ - የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - እጃቸውን ወደ ማዕዱ ከመስደዳቸውና ከመጀመራቸው በፊት እነርሱ እጃጀውን አይሰዱም ነበር። አንድ ቀን ከርሳቸው ጋር ማዕድ ለመጋራት ተገኘን። ከፍጥነቷ የተነሳ አመጣጧ ልክ እየተገፈተረች በሚመስል መልኩ የሆነች አንዲት ሴትዮ መጣችና እጇን ወደ ማዕዱ ሰደደች። የአላህ መልክተኛም - የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - እጇን ያዟት። ቀጥሎም ከፍጥነቱ የተነሳ አመጣጡ ልክ እየተገፈተረ በሚመስል መልኩ የሆነ አንድ የገጠር ሰውዬ መጣና እጁን ወደ ማዕዱ ሰደደ። የአላህ መልክተኛም - የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - ምግቡን ከመንካቱ በፊት እጁን ያዙትና እንዲህ አሉ: "ሰውዬው የአላህ ስም ሳይወሳበት ምግቡን የጀመረ ጊዜ ሸይጧን ምግቡን ለመመገብ ይመቻቻል። እርሱም ይህቺን ሴትዮ ምግቡን ለራሱ ለማስመቸት ይዟት መጣ። እጇንም ያዝኳት። ይህንንም ሰውዬ ምግቡን ለራሱ ለማስመቸት ይዞት መጣ። እጁንም ያዝኩት። ነፍሴ በእጁ በሆነው ጌታ እምላለሁ! የሸይጧንን እጅ ከሴትዮዋ እጅ ጋር በእጄ ነው።" ካሉ በኋላ የአላህን ስም ካወሱ በኋላ ተመገቡ።

ጥቅሞች

  • ሶሓቦች ለአላህ መልክተኛ - የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - የነበራቸውን ክብርና ከርሳቸው ጋር የነበራቸውን ስነ ስርዓት እንረዳለን።
  • ከምግብ ስነ-ስርዓቶች መካከል ልጆች ትላልቆችና የተከበሩ ሰዎች ምግቡን እስኪጀምሩ ድረስ መጠበቃቸው ነው።
  • ሸይጧን ፍላጎቱን ለማሳካት እንዲመቸው አንዳንድ ዝንጉ የሆኑ ሰዎችን ለሚያስደስተው ተግባራት እንደሚልክ እንረዳለን። ከነዚህም ውስጥ እዚህ ሐዲሥ ውስጥ የተጠቀሰው ይገኛል።
  • ነወዊይ እንዲህ ብለዋል: «ዑለማዎች እንዲህ ብለዋል: "ቢስሚላህ ሲሉ ሌላው እንዲሰማና እንዲያስታውስ ጮክ ብሎ ማለቱ ይወደዳል።"»
  • አንድ ሰው መብላት ፈልጎ ቢመጣና ቢስሚላህ ማለቱን ካልሰማህ ቢስሚላህ እስኪል ድረስ እጁን ያዘው።
  • አዋቂ የሆነ ሰው ውግዝ ተግባርን ማስተካከል ግዴታው ነው። አቅም ላለው ሰው ደግሞ ውግዝ ተግባርን በእጁ ማቀብ ግዴታው ነው።
  • ይህ ሐዲሥ ከአላህ መልክተኛ - የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - ተዓምራት መካከል አንዱ ተዓምር ነው። ይኸውም አላህ በዚህ ታሪክ ውስጥ የተከሰተውን ለርሳቸው ማሳወቁ ነው።
  • ሸይጧን የአላህ ስም ባልተጠራበት ወቅት ካልሆነ በቀር የኢማን ሰዎችን ምግብ ለመመገብ አይቻለውም።
  • ሰዎችን ኢስላማዊ የአመጋገብና የአጠጣጥ ስነ-ስርዓት ማስተማር ይወደዳል።
  • ሰሚው ዘንድ ጉዳዩን አፅንዖት ለመስጠት መማል እንደሚወደድ እንረዳለን።
  • ነወዊይ እንዲህ ብለዋል: "ውሃ፣ ወተት፣ ማር፣ መረቅ፣ መድሃኒትና ሌሎችንም መጠጦች በሚጠጣበት ወቅት ቢስሚላህ ማለት ልክ ምግብ ላይ ቢስሚላህ እንደማለት ነው።"
  • ነወዊይ እንዲህ ብለዋል: «ሆን ብሎም ይሁን ረስቶ ወይም ባለማወቅ ወይም ተገዶ ወይም ድንገት ባጋጠመው ሰበብ ተስኖት ምግቡን ሲጀምር ቢስሚላህ ማለትን ቢተውና ከዚያም መሃል ላይ ማለት ቢመቸው ቢስሚላህ ማለቱ ይወደድለታል። የሚለውም "ቢስሚላሂ አወለሁ ወአኺረህ" ነው። ይህም ነቢዩ - የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - እንዲህ ስላሉ ነው: "አንዳችሁ በሚመገብበት ወቅት የአላህን ስም ያውሳ። ሲጀምር የአላህን ስም ማውሳት ከረሳ ቢስሚላሂ አወለሁ ወአኺረሁ ይበል።" አቡዳውድና ቲርሚዚ ዘግበውታል።»

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

4 አንድ ጊዜ

ትርጉም እና ምንጭ

ከጃቢር ቢን ዐብደላህ (ረዲየሏሁ ዐንሁማ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እርሱ ነቢዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ሲሉ ሰማ: "አንድ ሰው ወደ ቤቱ ሲገባ በሚገባበት ወቅትም በሚበላበት ወቅትም አላህን ካወሳ ሰይጣን (ለባልደረቦቹ) 'ማደሪያም እራትም የላችሁም።' ይላል። በሚገባ ወቅት አላህን ሳያወሳ የገባ እንደሁ ሰይጣን 'ማደሪያ አግኝታችኋል' ይላል። በሚበላበት ወቅትም አላህን ካላወሳ ደግሞ 'ማደሪያም እራትም አግኝታችኋል።' ይላል።"

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ ( የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ቤት በሚገባ ወቅትና ምግብ ከመመገባችን በፊት አላህን ማውሳት አዘዙ። እርሱ ቤት በሚገባ ወቅትና ምግቡን በሚጀምር ወቅት አላህን (ቢስሚላህ) በማለት ያወሳ ጊዜ ሰይጣን ለግብረ አበሮቹ "እዚህ ባለቤቱ አላህን በማውሳት ከናንተ የተጠበቀበት በሆነው ቤት ውስጥ ምንም ማደሪያም እራትም የላችሁም።" ይላቸዋል። ሰውዬው ቤቱ በሚገባ ወቅትና ምግብ በሚመገብበት ወቅት አላህን ካላወሳ ግን ሰይጣን ለግብረአበሮቹ እዚህ ቤት ውስጥ ማደሪያም እራትም እንዳገኙ ይነግራቸዋል።

ጥቅሞች

  • ቤት በሚገቡበትና ምግብ በሚመገቡበት ወቅት አላህን ማውሳት እንደሚወደድ እንረዳለን። የቤቱ ባለቤቶች አላህን ካላወሱ ሰይጣን ቤቶች ውስጥም ያድራል፤ ከባለቤቶቹ ምግብም ይመገባል።
  • ሰይጣን የሰውን ልጅ በስራው፣ በእንቅስቃሴውና በሁሉም ጉዳዩ ይጠባበቀዋል። ሰው ከዚክር (ከውዳሴ) በተዘናጋ ጊዜ ሸይጧንም ከርሱ የሚፈልገው ፍላጎቱን ያገኛል።
  • ዚክር (ውዳሴ) ሰይጣንን እንደሚያባርር እንረዳለን።
  • ሁሉም ሰይጣን በንግግሩ የሚደሰቱና ትእዛዙን የሚከተሉት ተከታይና ወዳጆች እንዳሉት እንረዳለን።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

ጥያቄዎች

በዚህ ገጽ ላይ ምን አለ?

ከምግብ በፊት ዱዓ: እያንዳንዳቸው በዐረብኛ፣ ከትርጉማቸው፣ ከመጡበት ሐዲስ፣ ከደረጃቸው እና ከማብራሪያ ጋር።

ትርጉሞቹ ከየት ናቸው?

ከHadeethEnc.com፣ የተተረጎሙ የነቢዩ ሐዲሶች ኢንሳይክሎፒዲያ። እያንዳንዱ ሐዲስ እነሱ እንዳሳተሙት፣ ከምንጩ እና ከደረጃው ጋር እንዲሁም ወደ ዋናው የሚወስድ ማስፈንጠሪያ ይዞ ይቀርባል።

የዕለት ማስታወሻ ማግኘት እችላለሁ?

አዎ። ለAndroid የሆነው ነፃው የQabas መተግበሪያ የጠዋት እና የማታ ዚክርን በየቀኑ ያስታውስዎታል፣ ተመሳሳይ ቆጣሪም አለው።