ሲያስነጥሱ የሚባል ዱዓ እና መልሱ

ያስነጠሰው ሰው የሚለው እና የሰማው የሚመልሰው።

1 አንድ ጊዜ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሁረይራ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው: የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንዲህ ብለዋል: «"አንድ ሙስሊም በሌላ ሙስሊም ላይ ያሉት መብቶች ስድስት ናቸው።" ለርሳቸውም "የአላህ መልክተኛ ሆይ! ምን ምንድን ናቸው?" ተባሉ። እርሳቸውም "ያገኘኸው ጊዜ ሰላምታን አቅርብለት፤ የጠራህ ጊዜ ጥሪውን አክብር፤ ካንተ ምክርን በፈለገ ጊዜ ምከረው፤ አስነጥሶ አላህን ያመሰገነ ጊዜ "የርሐሙከሏህ" በለው፤ የታመመ ጊዜ ጠይቀው፤ የሞተም ጊዜ ቅበረው።"»

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና አንድ ሙስሊም በሌላ ሙስሊም ወንድሙ ላይ ካሉት ሐቆች መካከል ስድስቱን ጠቀሱ፡ የመጀመሪያው: ባገኘው ጊዜ "አስሰላሙ ዐለይኩም" (ሰላም በእናንተ ላይ ይሁን) በማለት ሰላምታውን ያቅርብለት። እርሱም "ወዐለይኩሙ-ስሰላም" በማለት ሰላምታውን ይመልስለት። ሁለተኛው: ለሰርግና ለሌሎች ድግሶች በጠራው ጊዜ ጥሪውን ማክበር ነው። ሶስተኛው: ምክር ባስፈለገው ጊዜ ያለምንም ማሞኘትና ማታለል መምከር ነው። አራተኛው: አስነጥሶ "አልሐምዱሊላህ" (ምስጋና ሁሉ ለአላህ የተገባው ነው) ያለ ጊዜ "የርሐሙከላህ" (አላህ ይዘንልህ፤ ይቅር ይበልህ) በማለት አስደስተው። እርሱም "የህዲኩሙሏህ ወዩስሊሕ ባለኩም" (አላህ ይምራህ፤ ጉዳይህንም ያስተካክልልህ) በማለት ይመልስ። አምስተኛው: በታመመ ጊዜ ይጠይቀው፤ ይጎብኘው። ስድስተኛው: በሞተ ጊዜ ይስገድበት፤ እስኪቀበር ድረስም ጀናዛውን ይከተለው።

ጥቅሞች

  • ሸውካኒይ እንዲህ ብለዋል: "(የሙስሊም ሐቅ) በማለት የተፈለገው መተዉ የማይገባ ማለት ነው። ይህንንም መፈፀም ወይ በግዴታ መልኩ ይሆናል፤ ወይም መተዉ በማይገባ ልክ አጽንዖት የተሰጠውና ግዴታን የሚመስል ተወዳጅ (መንዱብ) በሆነ መልኩ ይሆናል።
  • ሰላምታን መመለስ ሰላምታ የቀረበለት ሰው አንድ ሰው ከሆነ የነፍስ ወከፍ ግዴታ ይሆናል። በብዛት ለሆኑ ሰዎች ከሆነ ግን ስለ ሁሉም ሰላምታውን አንዱ ቢመልስ ራሱ በቂ ነው። ሰላምታን መጀመር ግን ከመሰረቱ ሱና ነው።
  • የታመመን መዘየር አንድ ሙስሊም በሙስሊም ወንድሞቹ ላይ ካሉት ሐቆች መካከል አንዱ ነው። ምክንያቱም ህመምተኛን መዘየር ቀልቡ ውስጥ ደስታና መፅናናትን ስለሚያመጣ ነው። ፈርዱ ኪፋያ (የተወሰኑ ሰዎች ከፈፀሙት በቂ የሚሆን) ግዴታም ናት።
  • ወንጀል እስካልሆነ ድረስ ጥሪን ማክበር ግዴታ ነው። ጥሪው ለሰርግ ድግስ ከሆነ አብዛኛው ዑለማዎች ሸሪዓዊ ምክንያት ኖሮት ካልቀረ በቀር ጥሪ ማክበሩ ግዴታ ነው ብለዋል። ከሰርግ ውጪ ለሆነ ጥሪ ከሆነ ግን አብዛኛው ዑለማዎች ጥሪ ማክበሩ ተወዳጅ (ሙስተሓብ) ነው ብለዋል።
  • አስነጣሹ አላህን ሲያመሰግን የሰማ ሰው አስነጣሹን "የርሐሙከሏህ" ማለቱ ግዴታ ነው።
  • የሸሪዓ ምሉዕነትና የማህበረሰቡን አንድነት፣ ኢማናቸውንና የውዴታቸውን ግንኙነት በመካከላቸው ለማስተሳሰር መጣሩን እንረዳለን።
  • (ፈሰምሚትሁ) የሚለው ዘገባም መጥቷል። በአንዳንዱ ደግሞ (ፈሸምሚትሁ) በሚል ተዘግቧል። ትርጉሙም በመልካምና በበረከት ዱዓ ማድረግ ነው። "ተሽሚት" ማለት አላህ የጠላት መደሰቻ ከመሆን ያርቅህ፤ ጠላትህን ከሚያስደስት ነገር ያርቅህ ማለት ነው። "ተስሚት" ማለት ደግሞ አላህ ወደ ቀጥተኛው መንገድ ይምራህ ማለት ነው።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

2 አንድ ጊዜ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: «የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ያስነጠሱ ጊዜ እጃቸውን ወይም ልብሳቸውን አፋቸው ላይ አድርገው ድምፃቸውን ይቀንሱበት ነበር።»

አቡዳውድ፣ ቲርሚዚና አሕመድ ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ያስነጠሱ ጊዜ:

መጀመሪያ: ከአፋቸው ወይም ከአፍንጫቸው አንዳች ነገር ወጥቶ አብሯቸው የተቀመጠውን ላለማወክ እጃቸውን ወይም ልብሳቸውን አፋቸው ላይ ያኖራሉ።

ሁለተኛ: ድምፃቸውን ይቀንሱ ነበር። ከፍም አያደርጉትም።

ጥቅሞች

  • በማስነጠስ ዙሪያ የነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) መመሪያ መገለፁና በዚህ ጉዳይ እርሳቸውን መከተል እንደሚገባ እንረዳለን።
  • አንድ ሰው ያስነጠሰ ጊዜ ከርሱ አንዳች ነገር ወጥቶ አብሮ የተቀመጠውን እንዳያውክ ልብስን ወይም መሀረብና የመሳሰሉትን አፍና አፍንጫ ላይ ማኖር እንደሚወደድ እንረዳለን።
  • ሲያስነጥሱ ድምፅን ዝግ ማድረግ የሚፈለግ ጉዳይ ነው። ይህም ስነ-ስርዓትን ከሚያሟሉና ከመልካም ስነ‐ምግባር የሚመደብ ነው።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

ጥያቄዎች

በዚህ ገጽ ላይ ምን አለ?

የማስነጠስ ዱዓ: እያንዳንዳቸው በዐረብኛ፣ ከትርጉማቸው፣ ከመጡበት ሐዲስ፣ ከደረጃቸው እና ከማብራሪያ ጋር።

ትርጉሞቹ ከየት ናቸው?

ከHadeethEnc.com፣ የተተረጎሙ የነቢዩ ሐዲሶች ኢንሳይክሎፒዲያ። እያንዳንዱ ሐዲስ እነሱ እንዳሳተሙት፣ ከምንጩ እና ከደረጃው ጋር እንዲሁም ወደ ዋናው የሚወስድ ማስፈንጠሪያ ይዞ ይቀርባል።

የዕለት ማስታወሻ ማግኘት እችላለሁ?

አዎ። ለAndroid የሆነው ነፃው የQabas መተግበሪያ የጠዋት እና የማታ ዚክርን በየቀኑ ያስታውስዎታል፣ ተመሳሳይ ቆጣሪም አለው።