ለሂዳያ እና ለጽኑ ልብ ዱዓ

ለሂዳያ፣ ለተቅዋ እና በኢማን ላይ ለሚጸና ልብ ዱዓዎች።

1 አንድ ጊዜ

اللَّهُمَّ اهْدِنِي وَسَدِّدْنِي

ትርጉም እና ምንጭ

ከዓሊይ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: «የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና እንዲህ አሉኝ: "'አሏሁመ‐ህዲኒ ወሰዲድኒ' (ትርጉሙም: አላህ ሆይ ምራኝ፣ አስተካክለኝም።) በልና መመራትን ከአሏህ ስትጠይቅ መንገድን መመራትን አስታውስ። መስተካከልን ስትጠይቅ ደሞ የቀስት ኢላማውን የማግኘት ያህል መገጠምን አስታውስ።"»

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ዓሊይ ቢን አቢ ጣሊብን (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - አላህን እንዲህ ብሎ እንዲጠይቅና እንዲለምን አዘዙት "አላህ ሆይ! ምራኝ" አቅናኝ፣ ጠቁመኝ "አስተካክለኝ" ግጠመኝ፣ በሁሉም ጉዳዮቼ የተቃና አድርገኝ።

ሁዳ (መመራት) ማለት እውነትን በዝርዝርም ሆነ በጥቅሉ ማወቅና እውነትን በግልፅም ሆነ በውስጥ ለመከተል መገጠም ማለት ነው።

ሰዳድ "መስተካከል" ማለት: በሁሉም ነገሮች በእውነት ላይ ትክክል በሚሆነው ቀጥ ማለትና መገጠም ማለት ነው። "ሰዳድ" ማለት በንግግርም፣ በተግባርም ሆነ በእምነት ቀጥተኛ የሆነ መንገድ ማለት ነው።

ሀሳባዊ ነገር በህዋሳዊ ነገሮች ይብራራሉና አንተ ይህን ዱዓ እያደረግክ "መመራትን ስትማፀን የመንገድ መመራትን" አስታውስ፤ ጉዞ የወጣ ሰው መንገድ መመራት እንደሚጠይቀው መመራት እየጠየቅክ እንደሆነ ቀልብህ ላይ አስቀምጥ። መንገድ የወጣ ሰው ከተመራው መንገድ ከመጥፋት ለመዳን ወደቀኝ ወይም ወደግራ ዘንበል አይልም። ቀጥ ብሎ በመሄዱም ሰላምን ያገኛልም ወደ አላማውም በፍጥነት ይደርሳል።

"መስተካከልን ስትጠይቅ ደሞ ቀስት ኢላማውን የማግኘትን ያህል መገጠምን አስታውስ።" አንተ ቀስት ስታነጣጥር በፍጥነት መድረሱንና ኢላማውን ማግኘቱ ላይ ነው የምታተኩረው። ቀስት ወርዋሪ ወደ አንድ ኢላማ ባነጣጠረ ወቅት ቀስቱን ወደ ኢላማው አስተካክሎ ያነጣጥራል። ልክ እንደዚሁ ያሰብከውን መገጠም እንደቀስቱ የተስተካከለ እንዲሆን አድርገህ ነው አላህን የምትጠይቀው። በጥያቄህም የፈለግከው የመመራትን ጥግና የመገጠምን ድካ ይሆናል ማለት ነው።

በዚህ ዱዓ ስትማፀን የምትፈልገውን ጉዳይ ቀስት ስትወረውር እንደምታልመው ትክክለኝነት እንዲሆን አላህን መገጠም ስትጠይቅ በቀልብህ ይህን ሀሳብ አስቀምጥ።

ጥቅሞች

  • ዱዓ አድራጊ ስራው እንዲስተካከልና እንዲቃና ሱናን በማጥበቅና ኒያን በማጥራት ላይ ሊጥር ይገባዋል።
  • ለመገጠምና ለመስተካከል በነዚህ ጠቅላይ ቃላቶች ዱዓ ማድረግ እንደሚወደድ እንረዳለን።
  • አንድ ባሪያ ለሁሉም ጉዳዮቹ በአላህ መታገዝ ይገባዋል።
  • በማስተማር ወቅት ምሳሌ ማድረግ እንደሚገባ እንረዳለን።
  • መመራትን፣ የሁኔታዎች መስተካከልን እና የአይን ርግብግቢት ያህል እንኳ ከርሱ ሳይጣመሙ መጨረሻ በማስተካከል በርሱ ላይ መዘውተርን አንድ ላይ ሰብስበው ዱዓእ ማድረጋቸውን እንረዳለን። "ምራኝ" የሚለው ቃል በመመራት ጎዳና ላይ የሚጓዝ መሆንን መጠየቅ ነው። "አስተካክለኝ" የሚለው ቃል ደግሞ ኢላማን ማግኘት፣ በመመራት ወቅት አለመጥመምን የሚጠቁም ነው።
  • ዱዓ አድራጊ በዱዓው ትኩረት ሊሰጥ፣ የዱዓውንም ትርጉም ወደ ቀልቡ ማቅረብ ይገባዋል። ይህም ዱዓው ተቀባይነት እንዲያገኝ ይረዳዋል።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

2 አንድ ጊዜ

اللهُمَّ إِنِّي أَسْأَلُكَ الْهُدَى وَالتُّقَى، وَالْعَفَافَ وَالْغِنَى

ትርጉም እና ምንጭ

ከዐብደላህ ቢን መስዑድ (ረዺየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው: ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ይሉ ነበር: "አላሁመ ኢንኒ አስአሉከል ሁዳ፣ ወትቱቃ፣ ወልዓፋፈ፣ ወልጊና" ትርጉሙም፡ "አላህ ሆይ! እኔ ቀናውን መንገድ፣ ጥንቁቅነትን፣ ጥብቅነትንና መብቃቃትን እጠይቅሃለሁ።" ማለት ነው።

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ከነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ዱዓዎች መካከል ይህ ዱዓ ይገኝበታል: "አልላሁመ ኢንኒ አስአሉከል ሁዳ" አላህ ሆይ! ሐቅን የማወቅና በሐቅ የመስራት ቀጥተኛውን መንገድ እጠይቅሃለሁ። "ወትቱቃ" ትእዛዛቶችህን ለመተግበርና ክልከላዎችህን ለመራቅ የሚረዳኝን ፍራቻህን እጠይቅሃለሁ። "ወልዐፋፍ" ከማይፈቀዱና መልካም ካልሆኑ ንግግሮችና ተግባራት ጥብቅ እንድታደርገኝ እጠይቅሃለሁ። "ወልጊና" ከጌታዬ በቀር ወደ አንድም ፍጡር የማልፈልግ እስክሆን ድረስ ከፍጡራን የተብቃቃ እንድታደርገኝ እጠይቅሃለሁ።

ጥቅሞች

  • እነዚህ ጉዳዮች የላቁ ጉዳዮች መሆናቸውን እንረዳለን። እነርሱም: ቀና መንገድ፣ ጥንቁቅነት፣ ጥብቅነትና የተብቃቃ ሰው መሆን ናቸው። እነዚህን ጉዳዮች በመላበስ ላይም መነሳሳቱን እንመረዳለን።
  • ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ለነፍሳቸው ጥቅምና ጉዳት ማምጣት አይችሉም። ይህንን የሚችለው አላህ ብቻ ነው።
  • ለፍጡራን መጥቀም፣ መጉዳትና መምራት የሚችለው አላህ ብቻ ነው። ከአላህ ውጪ ቅርብ መልዐክም፣ የተላከ ነቢይም ሆነ ከነርሱ ውጪ ያለ አካልም ቢሆን ማንም እነዚህን ማድረግ አይችልም።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

3 አንድ ጊዜ

اللهُمَّ أَصْلِحْ لِي دِينِي الَّذِي هُوَ عِصْمَةُ أَمْرِي، وَأَصْلِحْ لِي دُنْيَايَ الَّتِي فِيهَا مَعَاشِي، وَأَصْلِحْ لِي آخِرَتِي الَّتِي فِيهَا مَعَادِي، وَاجْعَلِ الْحَيَاةَ زِيَادَةً لِي فِي كُلِّ خَيْرٍ، وَاجْعَلِ الْمَوْتَ رَاحَةً لِي مِنْ كُلِّ شَرٍّ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአቡ ሁረይራ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: «የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና እንዲህ ይሉ ነበር: "አልላሁመ አስሊሕ ሊ ዲኒለዚ ሁወ ዒስመቱ አምሪ ወአስሊሕ ሊ ዱንያየለቲ ፊሃ መዓሺ፣ ወአስሊሕ ሊ አኺረቲለቲ ፊሃ መዓዲ፣ ወጅዐሊል ሐያተ ዚያደተን ሊ ፊ ኩሊ ኸይር፣ ወጅዐሊል መውተ ራሐተን ሊ ሚን ኩሊ ሸር"» ትርጉሙም "አላህ ሆይ! የነገሮቼ መጠበቂያ የሆነውን ሃይማኖቴን አስተካክልልኝ። በውስጧ ኑሮዬ የሆነውን ዱንያዬንም አስተካክልልኝ። መመለሻዬ የሆነውን የመጨረሻውን አለምም አስተካክልልኝ። ህይወቴን ሁሉንም መልካም ነገር የምጨምርበት አድርገው። ሞቴንም ከሁሉም መጥፎ ነገር የማርፍበት አድርገው።" ማለት ነው።

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ለመሙላት የተላኩለት የሆነውን የመልካም ስነምግባር መሰረቶችን የሰበሰበች ዱዓ አደረጉ። እነርሱም: የሃይማኖት፣ የዱንያና የመጨረሻው አለም መስተካከል ናቸው። በነዚህ አጠር ባሉ ቃላቶች የነዚህን ሶስቱንም ያጠቃለለ ጥቅምን አከታትለው ለመኑ። በቅድሚያ በሃይማኖት መስተካከል ጀመሩ። የሁለቱም ሀገሮች ሁኔታ የሚስተካከሉት በርሱ ነውና። እንዲህ አሉ:

(አላህ ሆይ! ሃይማኖቴን አስተካክለው።) በተሟላ መልኩ ስነስርዓቱን ጠብቄ እንድቆም ወፍቀኝ (አሳካልኝ)።

(የነገሮቼ መጠበቂያ የሆነውን) የጉዳዮቼ ባጠቃላይ ጠባቂ የሆነው ሃይማኖቴ ከተበላሸ ጉዳዮቼ ባጠቃላይ ይበላሻል፤ ባዶዬን እቀራለሁ፣ እከስራለሁ። እንዲስተካከል የተፈለገው የሃይማኖት ጉዳይም ዱንያ ስትስተካከል ካልሆነ በቀር ስለማይስተካከል እንዲህ አሉ:

(ዱንያዬን ለኔ አስተካክልልኝ) የሰውነት ጤና፣ ደህንነት፣ ሲሳይ፣ መልካም ሚስት፣ ጥሩ ዘር፣ ሐላል የሆነና አንተን ለማምለክ የሚያግዘኝን የሚያስፈልገኝን በመስጠት (ዱንያዬን ለኔ አስተካክልልኝ) ቀጥለው ዱንያቸው እንዲስተካከል የጠየቁበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ጠየቁ:

(በውስጧ ኑሮዬ የሆነውን) የኑሮዬና የህይወት ዘመኔ ስፍራ የሆነውን።

(መመለሻዬ የሆነውን የመጨረሻውን አለም አስተካክልልኝ።) አንተን ለመገናኘት የምመለስበት የሆነውን ማለት ነው። መጨረሻ የሚያምረውም ስራን በማስተካከልና አላህ ባሪያውን ለአምልኮ፣ ለኢኽላስና ለመልካም ፍፃሜ በመግጠሙ ነው።

ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና መጪው አለምን ከዱንያ በኋላ ያስከተሉት የመጀመሪያው አለም ለሁለተኛው አለም መስተካከል መዳረሻ ስለሆነ ነው። ዱኒያው አላህ በፈለገው መልኩ የተስተካከለለት ሰው መጪው አለምም ለርሱ ይስተካከልለታል በርሷም ውስጥ ይደሰታል።

(ህይወቴን አድርግ) የእድሜዬ መርዘምን (በሁሉም በኩል መልካም ነገር የምጨምርበት) መልካም ስራን የማበዛበት (ሞቴን አድርገው) መፍጠኑን (ከሁሉም መጥፎ ነገር የማርፍበት) ሞትን ከፈተናዎች፣ ከመከራ፣ የወንጀልና የዝንጉነት ፈተና ላይ ከመውደቅ፣ ከዱንያ ችግርና ጭንቀት የምገላገልበትና እረፍትን የማገኝበት አድርገው።

ጥቅሞች

  • ዲን ወሳኝ ነገር ነው። ስለዚህም ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ዱዓቸውን ከርሱ ጀመሩ።
  • ዲን ለሰው ልጅ ሁሉንም መጥፎ ነገር የሚከላከልለት መጠበቂያው ነው።
  • በዱኒያዊ ጉዳዮች ዱዓ የሚደረገው ዲንና መጪው አለም እንዲስተካከል ነው።
  • የዲን ፈተና በመፍራት ሞትን መመኘት ወይም አላህ ሸሂድ አድርጎ እንዲገድለው መጠየቅ አይጠላም።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

4 አንድ ጊዜ

يَا مُقَلِّبَ القُلُوبِ ثَبِّتْ قَلْبِي عَلَى دِينِكَ

ትርጉም እና ምንጭ

ከአነስ (ረዲየላሁ ዐንሁ) -አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው እንዲህ ብለዋል፦ «የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) "ያ ሙቀሊበል ቁሉብ ሠቢት ቀልቢ ዐላ ዲኒክ" (አንተ ልቦናን ገለባባጭ የሆንክ ጌታ ሆይ! ልቤን በሃይማኖትህ ላይ አፅናት) ማለትን ያበዙ ነበር። እኔም "የአላህ መልክተኛ ሆይ! በርሶና ይዘውት በመጡት ሃይማኖት አምነናል። በኛ ላይ የሚፈሩልን ጉዳይ አለ ማለት ነው?" አልኳቸው። እርሳቸውም "አዎን ልቦች በአላህ ሁለት ጣቶች መካከል ናቸው። እንደፈለገው ይገለባብጣታል።" አሉኝ።»

ቲርሚዚና አሕመድ ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

አብዛኛው የነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ዱዓ በኢስላምና በአምልኮ ላይ መፅናትንና ከጥመት መራቅን አላህን መጠየቅ ነበር። አነስ ቢን ማሊክም (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ይህን ዱዓ በማብዛታቸው ተደነቀ። ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ልቦች ከአላህ ጣቶች መካከል በሁለቱ ጣቶች መሀል እንደሆኑና እንደፈለገም እንደሚያገለባብጣቸው ነገሩት። ቀልብ የኢማንና ክህደት መኖሪያ ናት። ቀልብ ቀልብ ተብሎ የተሰየመው በብዛት ስለሚገለባበጥ ነው። ቀልብ ድስት በሚንተከተክ ጊዜ ከሚገለባበጠው በላይ ይገለባበጣል። አላህ ለሻለት ሰው ቀልቡን በቀናው መንገድ ላይና በኢስላም ላይ ያፀናለታል። አላህ ጥመት የሻለትን ሰው ደግሞ ቀልቡን ከቀናው መንገድ ወደ ጥመት ያዞርበታል።

ጥቅሞች

  • ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ለጌታቸው ያላቸው መዋደቅና መተናነስን እንዲሁም ኡመታቸውም ይህንን ጥያቄ እንዲጠይቁ መጠቆማቸውን እንረዳለን።
  • በኢስላም ላይ የመፅናትና ቀጥ የማለት አንገብጋቢነቱን እንረዳለን። ዋናው ቦታ የሚሰጠውም ፍፃሜያችን ነው።
  • አንድ ባሪያ በኢስላም ላይ መፅናትን ከአላህ ከመፈለግ ለአይን ጨረፍታ ያህል እንኳ አይብቃቃም።
  • ነቢዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ተከትለን ይህንን ዱዓ በማብዛት ላይ መነሳሳቱን እንረዳለን።
  • በእስልምና ላይ መፅናት አንድ ባሪያ ሊለፋለት የሚገባና በርሱም ጌታውን ሊያመሰግንበት የሚገባ ትልቁ ፀጋ ነው።

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

5 አንድ ጊዜ

ትርጉም እና ምንጭ

ከዐብደላህ ቢን ዐምር ቢን ዓስ -አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - የአላህን መልክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንዲህ ሲሉ ሰማ: "የአደም ልጆች ቀልቦች ሁሉ ከአርራሕማን ጣቶች በሁለቱ ጣቶች መካከል ናቸው። (እርሱ ዘንድ ሁሉም ቀልቦች) እንደ አንድ ቀልብ ናቸው። እንደፈለገ ይገለባብጣቸዋል።" ቀጥለውም የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንዲህ አሉ "ቀልቦችን አዘዋዋሪ የሆንከው አላህ ሆይ! ቀልባችንን በአምልኮህ ላይ አዙረው።"

ሙስሊም ዘግበውታል። ደረጃ: ሶሒሕ ነው።

ማብራሪያ

ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) የአደም ልጆች ሁሉ ቀልባቸው እንደ አንድ ቀልብ ከአርረሕማን ጣቶች በሁለት ጣቶቹ መካከል መሆናቸውን ተናገሩ። እንደፈለገውም ይገለባብጠዋል። ከፈለገ በሐቅ ላይ ያፀናዋል፤ ከፈለገም ከሐቅ ያጠመዋል። በሁሉም ቀልቦች ላይ የሚፈፅመው ማስተናበር የአንድ ሰውን ቀልብ እንደማስተናበር ነው። አላህን አንድ ጉዳይ ከሌላ ጉዳይ አያጠምደውም። ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ቀጥለው ይህን ዱዓ አደረጉ "አንዳንዴ ወደ ትእዛዝህ፣ አንዳንዴ አንተን ወደ መወንጀል፣ አንዳንዴ አንተን ወደማውሳት፣ አንዳንዴ ደሞ አንተን ከማውሳት ወደ መዘናጋት ቀልቦችን የምትገለባብጥ አላህ ሆይ! ልባችንን ወደ አምልኮህ አዙረው።"

ጥቅሞች

  • ቀደርን ማፅደቅ እንረዳለን። አላህ የባሮቹን ቀልብ በጻፈባቸው ውሳኔ ልክ ያዞራቸዋል።
  • አንድ ሙስሊም በእውነትና ቅናቻ ላይ ጌታው እንዲያፀናው አዘውትሮ መጠየቅ ይገባዋል።
  • አጋር በሌለው በአላህ ብቻ ቀልብን ማንጠልጠልና እርሱን ብቻ መፍራት እንደሚገባ እንረዳለን።
  • አጁርሪይ እንዲህ ብለዋል: "የሐቅ ባለቤቶች አላህ ነፍሱን በገለፀበት ነገር፣ መልክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አላህን በገለፁት ነገርና ሶሐቦች (ረዲየሏሁ ዐንሁም) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - አላህን በገለፁት ነገር ይገልፁታል።" ይህ ሐቁን የተከተሉና አዲስ ነገር ያልፈጠሩ ዑለማዎች መንገድ ነው።" (ንግግራቸው ተጠናቀቀ)። አህሉ ሱናዎች አላህ ለነፍሱ ያፀደቀውን ስሞችና ባህሪያት ሳያጣምሙ፣ ትርጉም አልባ ሳያደርጉ፣ አኳኋኑን ሳይገልፁና ሳያመሳስሉ ለአላህ ያፀድቃሉ። አላህ ከራሱ ላይ ውድቅ ያደረገውንም ነገር ውድቅ ያደርጋሉ። ማፅደቅም ሆነ ውድቅ ማድረግ ላልመጣበት ጉዳይም ዝም ይላሉ። አላህ እንዲህ ብሏል: {የሚመስለው ምንም ነገር የለም። እርሱም ሰሚው ተመልካች ነው።}"

በHadeethEnc.com ላይ ያንብቡ

ጥያቄዎች

በዚህ ገጽ ላይ ምን አለ?

የሂዳያ ዱዓ: እያንዳንዳቸው በዐረብኛ፣ ከትርጉማቸው፣ ከመጡበት ሐዲስ፣ ከደረጃቸው እና ከማብራሪያ ጋር።

ትርጉሞቹ ከየት ናቸው?

ከHadeethEnc.com፣ የተተረጎሙ የነቢዩ ሐዲሶች ኢንሳይክሎፒዲያ። እያንዳንዱ ሐዲስ እነሱ እንዳሳተሙት፣ ከምንጩ እና ከደረጃው ጋር እንዲሁም ወደ ዋናው የሚወስድ ማስፈንጠሪያ ይዞ ይቀርባል።

የዕለት ማስታወሻ ማግኘት እችላለሁ?

አዎ። ለAndroid የሆነው ነፃው የQabas መተግበሪያ የጠዋት እና የማታ ዚክርን በየቀኑ ያስታውስዎታል፣ ተመሳሳይ ቆጣሪም አለው።